አርዕስተ ዜና

የህትመት ውጤቶችን የማንበብ ባህል ተቀዛቅዟል- አስተያየት የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች

339 times

የካቲት 6/2010 የኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋትና የመጻህፍት ዋጋ መናር  የህትመት ውጤቶችን የማንበብ ባህል እንዲቀንስ ማድረጉን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ወጣት ፍቃዱ ወንድሙ እንደተናገረው የኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋቱ በአነስተኛ ወጪ የእጅ ስልኩን ተጠቅሞ መረጃዎችን በቀላሉ ለማውረድ አግዞታል፡፡ ይህ ደግሞ  የህትመት ውጤቶችን የማንበብ ባህሉ እንዲቀዛቀዝ እንዳደረገው ነው የተናገረው፡፡

መጻህፍትን ገዝቶ የማንበብ ልምድ እንደነበረው የተናገረው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሰለሞን አየለም የመጻህፍት ዋጋ ንረቱ የማንበብ ፍላጎቱን እንደገታበት ተናግሯል፡፡

ተማሪ ሰላማዊት ዘሪሁን ደግሞ መጻህፍትን እየተከራየች የማንበብ ልምዱ ቢኖራትም  የመጻህፍት ኪራይ አገልግሎቱ በመቋረጡ አዳዲስ መጻህፍትን በቀላሉ ማግኘት አልቻለችም፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አብያተ መጻህፍትም በአዳዲስና አጋዥ መጻህፍት ባለመደራጀታቸው ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት መቸገሯን ነው የገለጸችው፡፡

ጊዮርጊስ አካባቢ መጽሀፍ በማከፋፈልና በመቸርቸር ስራ የተሰማራው አብዱልመጂድ ሁሴን እንደሚለው የህብረተሰቡ መጽሀፍ ገዝቶ የማንበብ ባህል አንጻራዊ ለውጥ ቢታይበትም ገበያው ግን እንደተቀዛቀዘ ነው፡፡

በእውቅ ደራሲ የተጻፈ ወይም አዲስ ነገር የያዘ መጽሃፍ በውድ ዋጋ ገዝተው የሚያነቡ ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም አብዛኛው ሰው ግን የዋጋውን ውድነት አይቶ እየሸሸ መሆኑን የተናገረው ደግሞ  አራት ኪሎ አካባቢ መጽሃፍ የሚሸጠው ቢቀርብኝ ተሻለ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝምና ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ መንገሻ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ አብያተ መጻህፍት በአሮጌ መጻህፍት የተሞሉ በመሆናቸው አንባቢው ርቋቸው ቆይተዋል፡፡

ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ግን በየአመቱ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ  የህብረተሰቡን አስተያየት መሰረት በማድረግ  አብያተ መጻህፍቱን በአዳዲስ መጻህፍት የማደራጀትና አዳዲስ አብያተ መጻህፍትን የመክፈት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየአብያተ መጻህፍቱ ተቀምጠው ማንበብ ለማይችሉ መጽሃፍ የማዋስ፣  በሆስፐታልና ወህኒ ለሚገኙ ሰዎች ደግሞ ተንቀሳቃሽ የቤተ መጻህፍት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በአስሩ ክፍለ ከተሞችና  በማእከል የሚገኝ አንድ ቤተ መጻህፍትን በኔትወርክ በማስተሳሰር አገልግሎቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ አድርጓል፡፡

በበጀት አመቱ ማጠናቀቂያ ደግሞ  በየካ ክፍለ ከተማ  ባለ አራት ፎቅ አዲስ ዘመናዊ የንባብ ማእከል ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች  እየተሰሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

Last modified on Wednesday, 14 February 2018 00:15
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን