አርዕስተ ዜና

በመጠጥ ውሀ እጥረት መቸገራቸውን የሚኤሶና ጭሮ ነዋሪዎች ገለጹ

424 times

ጭሮ የካቲት 6/2010 በአካባቢያቸው ባጋጠማቸው የንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶና ጭሮ ወረዳዎች አስተያየታቸውን የሰጡ  ነዋሪዎች ገለጹ።

በጭሮ ወረዳ የጋራንጉስ  ቁጥር ሁለት ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ሙሉካ ዩያ እንዳሉት በአካባቢው ጎልብቶ የነበረው  ምንጭ በመድረቁ የሶስት ሰዓት መንገድ በመጓዝ የኩሬ ውሃ  እየቀዱ ለመጠቀም ተገደዋል።

"ከነ ቤተሰቤ ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ ለመጠጣት በመገደዳችን  ለውሀ ወለድ በሽታ ተጋልጠናል" ያሉት ወይዘሮ ሙሉካ ችግሩ በተለይ በህጻናት ላይ እንደሚብስ ተናግረዋል ።

መምህር ካሳሁን መርጋ በበኩላቸው የንፁህ መጠጥ ውሀ እጦት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

"መምሀራን አንድ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ውሃ በ20 ብር እየገዛን እየተጠቀምን ነው " ያሉት መምህሩ ወሀ ፍለጋ በየእለቱ ረዥም መንገድ በመጓዝ  የመማር ማስተማር ስራው እየተስተጓጎለ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በሚኤሶ ወረዳ የሁሴ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ ብርሃን ኪዳኑ እንደገለጸው  ቤተሰቦቹን ለመርዳት ንጽህ የውሃ ለመቅዳት ሲል ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል።

በወረዳው የሀሙስ ገበያ ጤና ጣቢያ ሲስተር ኢየሩስ ደምሴ በሰጡት አስተያየት በየቀኑ ከሚመጡ ታካሚዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ንፅህናው ባልተጠበቀ ውሀ በመጠጣት ህመም ያጋጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጁዋር ጠሃ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው የውሀ ችግር በመኢሶና ጭሮ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወረዳዎች መኖሩን ገልጸዋል።

በወረዳዎቹ  ከዚህ ቀደም  የጎለበቱ ምንጮች ውሀ የማመንጨት አቅማቸው በመቀነሱ ችግሩ መከሰቱን ጠቁመዋል ።

"ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በሁለቱም የወረዳ ቀበሌዎች የተጀመሩ የአንድ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና የአንድ ምንጭ ማጎልበት ስራዎች በበጀት እጥረት መቋረጣቸው ለውሀ እጦቱ መባባስ ሌላው ምክንያት ነው" ብለዋል ።

ችግሩ በከፋባቸው ቦታዎች ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት አስር ቦቴ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው የውሀ እደላ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ አቶ ጁዋር ገለጿ የተቋረጠውን የውሀ ተቋማት ስራ ለማስጀመር ለኦሮሚያ  የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ የበጀት ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን