አርዕስተ ዜና

የአዳማን ፅዳትና ውበት ለመጠበቅ ሴቶችና ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩ ነው

352 times

አዳማ የካቲት 6/2010 የአዳማ ከተማን ፅዱ፣ውብና አረንጓዴነት ለመጠበቅ  ሴቶችና ወጣቶችን በማሳተፍ እየሰራ እንደሚገኝ የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።

አስተዳደሩ በከተማዋ ፅዳት፣ውበትና አረንጓዴ ልማት ሥራ ተሰማርተው ውጤታማ ለሆኑ 20 የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት  የገንዘብ ሽልማትና እውቅና ሰጥቷል።

በዚሁ ወቅት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ እንደገለጹት በከተማዋ የሚታየው የፅዳት ችግር ለዘመናት የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡

"የከተማዋን የቱሪዝም ኮንፈረንስ፣ የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከልነት ለማረጋገጥ ፅዱ፣ውብና አረንጓዴ ማድረግ ይጠበቅብናል "ብለዋል።

አስተዳደሩ የከተማዋን ፅዳት፣ውብና አረንጓዴ ልማት ሥራን 1ሺህ 144 አባላት ያሏቸውን  110 የሴቶችና ወጣቶችን በማህበራት አደራጅቶ በዘርፉ በማሰማራቱ  መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከተማዋ ከአዲስ አበባ ቀጥላ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት መሆኗን ጠቅሰው የአዳማን  ፅዳት፣ውበትና ለምነቷን መጠበቅ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ተመራጭ መሆን እንደሚያስችላት ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው ማህበራት መካከል የሃጫሉ ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ሸዋዬ ዘርፉ " አስተዳደሩ አደራጅቶን ሥራ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ለልጆቻችን ቀለብ፣አልባሳትና የትምህርት ወጪያቸውን ለመሸፈን እንቸገር ነበር" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከስራው በሚያገኙት ገቢ የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ችግር ሳይገጥማቸው ልጆቻቸውን  እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡

በቀጣይነት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ  ወይዘሮ ሸዋዬ ተናግረዋል።

"መንግስት የከተማዋን ፅዳትና ውበት  ለማስጠበቅ በዘረጋው የሥራ አማራጭ ተሰማርተን ህይወታችንን መለወጥ ችለናል "ያሉት ደግሞ የአዲስ ራዕይ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ ባዩ ናቸው።

ማህበራቸው ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ በመቀየር ለከተማዋ መስተዳደርና ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አንድ ሜትር ኪዩብ በ185 ብር እያስረከበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በቀጣይም  ምርታቸውን ለአካባቢው አርሶ አደሮች ለማቅረብ እቅድ ይዘው እየሰሩ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

Last modified on Tuesday, 13 February 2018 20:36
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን