አርዕስተ ዜና

የሸገር ትራንስፖርት አገልግሎት የአርፋጅና ቀሪ ተማሪዎችን ቁጥር ቀንሶታል

336 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 ሸገር ትራንስፖርት ለተማሪዎች አገልግሎት በጀመረባቸው መስመሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአርፋጅና ቀሪ ተማሪዎች ቁጥር መቀነሱ ተነገረ።

የተማሪዎች ብቻ የሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታም ፈጥሯል ተብሏል።

የሰላም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ በእምነት ሳሙኤል ከመኖሪያ አካባቢዋ የካ አባዶ ተነስታ ትምህርት ቤቷ ለመድረስ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ በትራንስፖርት ትጓዛለች።

ተማሪዋ ከቤቷ ተነስታ ትምህርት ቤት ለመድረስ ከሁለት ሠዓት በላይ የታክሲ ሰልፍ መያዝና መጉላላት ይደርስባት ነበር።

በዚህ ሳቢያም ከትምህርት ገበታዋ አርፍዳ መግባት፣ ባስ ሲልም እስከ መቅረት ትደርስ እንደነበር ለኢዜአ ገልጻለች።

ታክሲ በመጠበቅ በሚፈጠርባት የድካም ስሜት ትምህርቷን ለመከታተል ትቸገር እንደነበርና በሠዓቱ ባለመድረሷም ትምህርት እንደሚያመልጣት ታስታውሳለች።

በቅርቡ የተጀመረው የሸገር የተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በትምህርት ገበታዋ ላይ በሠዓቷ መገኘት እንዳስቻላት ተናግራለች።

የአገልግሎቱ መጀመሩ ቀደም ሲል በትራንስፖርት ጥበቃ ታባክነው የነበረውን ጊዜ፣ ገንዘብና እንግልት እንዳስቀረላትም አክላለች።

የሂልሳይድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዮናታን ዳግም በበኩሉ ወደ ትምህርት ቤት ለመመላለስ ወላጆቹ ለኮንትራት ታክሲ ያወጡት የነበረው ገንዘብ ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳል።

የሸገር ትራንስፖርት አገልግሎት በመጀመሩ ወጪውን በግማሽ እንደቀነሰውና ጊዜውንም እንደቆጠበለት ተናግሯል።

ከአውቶቡሶቹ ምቾት ባሻገር ደህንነቱ መጠበቁንና የትራፊክ አደጋ ስጋቱም እንደቀነሰለት ገልጿል ዮናታን።

ይደርስባቸው የነበረው እንግልት ቀርቶ ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸውም አክሏል። 

የሰላም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ኃይለማርያም ካሳ በበኩላቸው የትራንስፖርት አገልግሎቱ  ከመጀመሩ በፊት የአርፋጅ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

አገልግሎቱ የተማሪዎችን ልፋት በመቀነስ ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።

ሆኖም አገልግሎቱ የሚሰጠው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ለሆኑ ተማሪዎች ብቻ መሆኑ በሌሎች ተማሪዎች ላይ ቅሬታ እያሳደረ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ቢሰጠው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

በሸገር ብዝሃ ትራንስፖርት ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪና አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ፍሰሃ ድርጅቱ በትራንስፖርት እጦት በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለማስቀረት በተመረጡ መስመሮች በ30 አውቶቡሶች አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል።

በምርት ሂደት ላይ የሚገኙት 70 አውቶቡሶች ወደ ስራ ሲገቡ በተደራሽነት ላይ የሚነሳው ቅሬታ ይቀንሳል ነው ያሉት።

በአገልግሎቱ ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚደረጉም አቶ ሳሙኤል አስታውቀዋል።

ሸገር ብዝሃ ትራንስፖርት ድርጅት በአዲስ አበባ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 70/2008 የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን