አርዕስተ ዜና

የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት በዓለ ዝክር ተጠናቀቀ

155 times

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2010 ባለፈው ወር በቋራ የተጀመረው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት በዓለ ዝክር ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደ ሲምፖዚየም ተጠቃለለ።

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ባለውለታውን አፄ ቴዎድሮስን የሚያስታውስ መነባንብ፣ የልጃቸው ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን ታሪክ የሚዳስሱ ፅሁፎችና ከመቅደላ አምባ የተዘረፉ ቅርሶች ለእይታ ቀርበዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው ይህ የመታሰቢያ በዓል ከመጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ከንጉሡ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካባቢዎች በመጎብኘትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ምሁራን በውይይት ሲያስቡት ሰንብተዋል።

በዛሬው መርሃ ግብር የታደሙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ጀግናው ንጉሥ በህይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ልማት ያደረጉትን ጥረት አውስተዋል።

የጀመሯቸውን የለውጥና የነፃነት ሃሳብና ተግባራት ከእሳቸው በኋላ የተነሱትም ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደተወጡም መስክረዋል።

አሁንም መንግስት ልማትና አንድነትን መሰረታዊ የመለወጥ ጉዳይ አድርጎ መነሳቱ ቴዎድሮስ ጀምረውት የነበረውን ራዕይ የማስቀጠል መነሻ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳሁን በበኩላቸው አፄ ቴዎድሮስ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት የሆኑ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጊዜው ይናቁ የነበሩትን የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች በማበረታታት ለዘመናዊ ኢንዱስትሪ መጀመር መነሻ የሆነውን ሴባስቶፖልን ማሰራታቸውንም አስታውሰዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለፃ ባለታሪክ የሆኑ ጀግኖች ሲዘከሩ የሰሯቸውን መልካም ስራዎች በላቀ ሁኔታ በማስቀጠል እንከኖቻቸውም ለይቅርታና ለትምህርት በሚሆን መልኩ ሊተረጎሙ ይገባል ነው ያሉት።

ለትውልዱ የማንነት ማስተማሪያ፣ የአንድነት ተምሳሌቶችና የኢትዮጵያዊነት ኩራቶች የሆኑ ጀግኖችን በዚህ መልክ ለትውልዱ መዘከር ለአገራዊ ስሜት መነሳሳት መልካም አጋጣሚ ነውም ብለዋል።

በመቅደላ አምባ ንጉሡ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ከገደሉ በኋላ በእንግሊዞች በርካታ ቅርሶች የተዘረፉ ሲሆን እንዚህን ማስመለስ በሚቻልባቸው ሂደቶች ላይ የመንግስትና የህብረተሰቡ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ለዳግማዊ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ማዘጋጀታቸውም ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አብነት እንደሚሆን ተነግሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ አርቲስት ሱራፌል ተካ ከአፄ ቴዎድሮስ ቴአትር የተቀነጨበውንና ንጉሡ በመቅደላ አምባ ያደረጉትን የመጨረሻ ንግግርና ሞታቸውን የሚያሳየውን ክፍል ለታዳሚው አቅርቧል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን