አርዕስተ ዜና

የመሬት ካሳ ክፍያና የምትክ ቦታ አሰጣጥ ችግሮች የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲን የህንጻ ግንባታ አዘግይተውታል ተባለ

141 times

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 8/2010 ለአርሶ አደሮች መፈጸም ያለባቸው የመሬት ካሳ ክፍያና የምትክ ቦታ አሰጣጥ ችግሮች ለኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የህንጻ ግንባታዎች መዘግየት ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገለጸ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዩኒቨርሲቲው የ2010 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ በአራተኛው ዙር ከተቋቋሙ 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ጭሮ ይገኛል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙክታር መሃመድ እንደገለፁት በ2008 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው ከ20 በላይ ህንጻዎች ግንባታ ለመጀመር እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።

ሆኖም ግንባታዎቹ በሚከናወኑባቸው ቦታዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከሚፈጸሙ የካሳ ክፍያዎችና ከሚሰጡ ምትክ ቦታዎች ጋር በተያያዘ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጊዜ በመውሰዱ ግንባታውነ በታቀደው ጊዜ ለመጀመር አልተቻለም ብለዋል።

እንደ ዶክተር ሙክታር ገለጻ በትምህርት ሚኒስቴር ለ200 ሄክታር መሬት ካሳ ክፍያ 20 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደር ደግሞ ለ164 ሄክታር ወደ 300 ሚሊዮን ብር ግምት ቀርቧል።

በመሬት ካሳ ክፍያ ግምቱ ከፍተኛ ልዩነት ሳቢያ ተጨማሪ በጀት በማስፈለጉ የካሳ ክፍያ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጊዜ ፈጅቷል።

በአሁኑ ወቅት የሕብረተሰቡ ቅሬታዎች ሙሉ ለሙሉ ባይፈቱም ከታቀዱት ግንባታዎች የተወሰኑት ህንጻዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አብዛኞቹን ግንባታዎች በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ላይ ለማጠናቀቅና ተማሪዎችን ለመቀበል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ይህን ለማሳካትም ጉዳዩ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደር፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማትና በትምህርት ሚኒስቴሮች ልዩ ትኩረት የሚያገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከቋሚ ኮሚቴው እገዛ እንዲያደረግላቸው ዶክተሩ ጠይቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥና በአካባቢው ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የትምህርት ጊዜ መስተጓጎሉ፣ ለግዢ የሚቀርቡ ዕቃዎች በወቅቱ ያለመቅረብ፣ የመማሪያ ክፍሎችና ቢሮዎች እጥረትና 3ኛ ዲግሪ ያላቸውን መምህራን በበቂ ሁኔታ ያለማግኘት ችግሮች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያጋጠሙ ችግሮች ሲሉም  ጠቅሰዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ዋቅጅራ ተርፋሳ ዩኒቨርሲቲው ከግንባታ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ከስራ አመራር ቦርዱ ጋር በቅርበት መስራት እንደሚገባው ገልጸው ቋሚ ኮሚቴውም እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የተማሪዎችን አደረጃጀት በመጠቀም ሠላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የመምህራን የትምህርት ደረጃ ወሳኝ በመሆኑ ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸውን መምህራን ቁጥር ለማሳደግ ጥረት ማድረግም ይገባል ነው ያሉት።

የሴት መምህራንን ቁጥር ለማሳደግና ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣትም ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን