አርዕስተ ዜና

ቋሚ ኮሚቴው በአዲስ አባባ ከተማ የሚገኙ ወጣት ማዕከላት ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ እንዳልሆነ አመለከተ

135 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመዲናዋ የሚገኙ የወጣት ማዕከላት ለተቋቋሙለት ዓላማ እየዋሉ አለመሆኑን ገለጸ።

ኮሚቴው ባደረገው ምልከታ በመዲናዋ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የወጣት ማዕከላት የግለሰቦች መጠቀሚያ እየሆኑ እንደሚገኙ አረጋግጧል።

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ አሰጣጥ ፍትሃዊነት እንደሚጎድለውም ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ምልከታው ማረጋገጡን ገልጿል።

ቋሚ ኮሚቴው የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮን የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲሃ መሃመድ እንደተናገሩት፤ መንግስት በመዲናዋ ለወጣቶች መዝናኛነት ያስገነባቸው በርካታ የወጣት ማዕከላት ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ነገር ግን እነዚህ ማዕከላት የተደራጁ ወጣቶች እንዲሰሩባቸው የተቋቋሙ ቢሆንም በአብዛኛው የግለሰቦች መጠቀሚያ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ማዕከላቱ በህገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች በኪራይ መልኩ እየተላለፉ የኪራይ ሰብሳቢዎች ሰለባ ሆነዋል።

አንዳንድ የወረዳ አመራሮች ከባለሃብቶች ጋር በመመሳጠር ከወጣቶች ውጪ ሌሎች እንዲጠቀሙበት ማድረጋቸውን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በወጣቶች ማዕከላት ላይ የሚያደርገው ክትትል ክፍተት ያለበት በመሆኑ ትኩረት በመስጠት ማዕከላቱ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በሌላ በኩል መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመደበው የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ አቅርቦት የሚታየው ፍትሃዊ ያልሆነ ተጠቃሚነት ሊስተካከል እንደሚገባ ወይዘሮ ፈቲሃ አስገንዝበዋል።

ይህም ወጣቶቹ ተደራጅተው ብድር ሊወስዱ በሚሄዱበት ጊዜ በብድር ሰጭው ተቋም ሰራተኞች የመልካም አስተዳድር ችግር እንደሚደርስባቸው በምልከታ መረጋገጡን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ብድር በሚጠይቁበት ጊዜ ከተቀመጠው መስፈርት ውጭ የቤት ካርታ፣ የመኪና ሊብሬና ሌሎች መደለያዎች እንደሚጠየቁ ገልጸዋል።

ይህ አሰራር በወጣቱ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥርና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍት በመሆኑ ቢሮው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ አርዓያ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 113 የወጣት ማዕከላት በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ አምነዋል።

ማዕከላቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ያለባቸውን ችግር የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከነዚህም መካከል በዚህ ዓመት ችግር አለባቸው የተባሉ 23 ወጣት ማዕከላት ከተፈቀደው ጊዜ በላይ ይዘው እየተገለገሉ የነበሩ ሰዎችን በማስለቀቅ ለሌሎች ወጣቶች የማስተላለፍ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በወጣቶቸ ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ላይ የሚነሳውን ቅሬታ በተመለከተ ቢሮው ከወጣቶች ጋር ውይይት በማድረግ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን