አርዕስተ ዜና

ሆስፒታሉ ለህፃናት የደምና የካንሰር ህክምና አገልግሎትን ለማዳረስ የህብረተሰቡን ድጋፍ ጠየቀ

318 times

መቀሌ ሚያዝያ 7/2010 በመቀሌ ዩኒቨርስቲ  የዓይደር አጠቃላይ  ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  የህፃናትን የደምና የካንሰር ህክምና   አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የህብረተሰቡን ድጋፍ ጠየቀ፡፡

 በሆስፒታሉ የህፃናት የደምና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ታደለ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለፁት ተቋሙ ለህፃናት የደምና የካንሰር ህክምና   አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ዘጠኝ ወራት ሆኖታል፡፡

 ይህም  አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ አገልግሎቱ መሰጠቱ የነበረን የጉዞ ምልልስ በማስቀረት ህሙማኑን  ለመርዳት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አሁንም የህክምና ወጪው   ከአብዛኛዎቹ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች አቅም  በላይ እንደሆነ ዶክተር ታደለ ተናግረዋል፡፡

 ሆስፒታሉ በህጻናት የሚታየውን የደም መርጋት፣ መፍሰስ ፣ ማነስ ፣ የቀይ ደም ሴሎች ማለቅ ህክምና የነጭ ደም መቆጣት ህክምና መስጠት ጀምሯል፡፡በሌላ በኩል የካንሰር ህክምናን በውስን የሰው ኃይል አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

  ህጻናቱ ህክምናውን አግኝተው ለመዳን  ከሁለት ዓመት በላይ በመፍጀቱ በችግር ምክንያት ታካሚዎች ህክምናውን ሳይጨርሱ የሚያቋርጡትን ለመታደግ  ህብረተሰቡ ደም ከመለገስ ጀምሮ የሚችለውን ያህል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

 መንግስት የመድኃኒት ድጎማ የሚያደርግ ቢሆንም ዋጋው ውድ በመሆኑ የባለሀብቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ ማስፈለጉንም ጠቁመዋል፡፡

 ሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ሁለት መቶ የሚሆኑ በደም ማነስና በሌሎች የደም ችግሮች ታምሞው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

 የካንሰር ህክምና አገልግሎት ካገኙት  ህጻናት መካከል ህጻን እጠፋኖስ  አብረሀ አንዱ ነው፡፡

 የህጻኑ አባት አቶ አብረሀ ከበደ እንዳሉት ልጃቸውን ለማሳከም ሁለት ዓመት ሙሉ ወደ ሆስፒታሉ መመላለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

 ልጃቸው በዓይደር ሆስፒታል ታክሞ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ከበደ" ለመድኃኒት መግዣ የሚወጣው ወጪ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ይከብዳቸዋል" ብለዋል፡፡

 ከአላማጣ አካባቢ የመጡ ወይዘሮ ቆንጂት ረታ በበኩላቸው የልጃቸውን በሽታ ባለማወቅ ስጋት ላይ ወድቀው እንደነበር ገልጸው አሁን ልጃቸው በተደረገለት የህክምና እርዳታ በመልካም ጤንነት  ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን