አርዕስተ ዜና

በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆናቸውን በጋሞ ጎፋ ዞን የተደራጁ ሴቶች ገለጹ

317 times

አርባ ምንጭ ሚያዝያ 7/2010 በማህበር ተደራጅተው የተሰማሩበት ሰራ መስክ ውጤታማ መሆናቸውን በጋሞጎፋ ዞን በዲታና ካምባ ወረዳዎች  ሴቶች ገለፁ።

በዲታ ወረዳ የሌሻ ቀበሌ ሴቶች ማህበር  ሰብሳቢ ወይዘሮ ኦቢቴ ኦኖ ለኢዜአ እንዳሉት  191 የማህበሩ አባላት 2008 ዓ.ም ተደራጅተው በግብርና ስራ ተሰማርተዋል ።

"በተሰጠን ሶስት ሄክታር መሬት ላይ ድንች፣ አተር፣ ባቄላና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ከምናገኘው ገቢ በማህበሩ ስም 100 ሺህ ብር ቆጥበናል " ብለዋል ።

አባላቱ በተያዘው ዓመት ከምርት ሽያጭ ከ10 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከማህበሩ በብድር  ባገኙት ገንዘብ የሳር ክዳን ቤታቸውን በቆርቆሮ መቀየራቸውን የገለፁት ወይዘሮ ኦቢቴ ከጠባቂነት ተላቀው ባለቤታቸውን በወጪ እያገዙ ናቸው።

በካምባ ወረዳ ኡጹማ ቀበሌ ዕድገት በህብረት ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር ያቻ በበኩላቸው 135 የማህበሩ አባላት በዶሮ እርባታና የጓሮ አትክልት ልማት በ2009 ዓ.ም ተደራጅተዋል ።

"አባላቱ በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ በመሆን ከምርት ሽያጭ ካገኘነው ገቢ ከ160 ሺህ ብር በላይ ቆጥበናል" ብለዋል ።

ያልተማሩ የማህበሩ አባላት የመፃፍና የማንበብ ክህሎት እንዲያዳብሩ  ዘንድሮ የተግባር ተኮር ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በዞኑ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ ወይዘሮ በላይነሽ በቀለ ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ሴቶች ተደራጅተው በብድርና ቁጠባ አገልግሎት  ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣቱን ተናግረዋል።

"በማህበር የተደራጁ ሴቶች 12 ሚሊዮን ብር ብድር ተሰጥታቸው የተሰማሩባቸውን የግብርና ስራዎች እያሰፋፉና እያጠናከሩ ናቸው" ብለዋል ።

በዞኑ 15 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከ12 ሺህ በላይ ሴቶች 265 የብድርና ቁጠባ ማህበራት አቋቁመው ከ4 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማፍራታቸውን ጠቅሰዋል ።

ሴቶቹ የቆጠቡትን ሶስት እጥፍ የብድር አገልግሎት በማግኘት በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ተሰማርተዋል፡፡

በዞኑ ተጨማሪ 255 የሴቶች ማህበራትን ለማቋቋም  ታቅዶ እየተሰራ ነው ።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን