አርዕስተ ዜና

ታሪካዊው የመቅደላ አምባ የተጠናከረ አካባቢ ጥበቃና መልሶ ግንባታ ያስፈልገዋል -ምሁራን

300 times

ደሴ ሚያዝያ 7/2010 ታሪካዊው መቅደላ አምባን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተጠናከረ አካባቢ ጥበቃና መልሶ ግንባታ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ፡፡

 የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ ህይወታቸው ያለፈበት የመቅደላ አምባ ተራራን የአውሮፓ  ምሁራን ትናንት ጎብኝተዋል፡፡

 ከምሁራኑ መካከል የህጻናት መጽሐፍ ደራሲ ዌልሳዊቷ ሄለን ፓፕወርዝ ጉብኝቱን  አስመልክታ እንደተናገረችው በ1868 እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር  ከኒዮርክ ሄራልድ ጋዜጣ ጦርነቱን ለመዘገብ ከዌልስ ወደ መቅደላ ተጉዞ የነበረውን ሄንሪ ሞርተን ስታንሌይ አስታውሰዋል፡፡

 ዘጋቢው " ኮማሲ ኤንድ መቅደላ" በሚል ባዘጋጀው መጽሐፉ  ጦርነቱንና የአጼ ቴዎድሮስን አሳዛኝ ፍጻሜ ለማወቅ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

 በአውሮፓ  አጼ ቴዎድሮስም ሆኑ መቅደላ አምባ የገዘፈ ስም እንዳላቸው ያወሱት ምሁሩ ይህ ታሪካዊ ጀግና የተዋጉበትና ያረፉበት ቦታ በሚጠበቀው ደረጃ የቱሪስት መዳረሻ ሳይሆኑ እንደቆየ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

 መቅደላ አምባ ታሪካዊነቱን ሳይለቅ በኤኮ ቱሪዝም መጠናከር እንዳለበት የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዋ  ወደ ታሪካዊው ስፍራ መዳረሻ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

 "በጦርነቱ ወደ እንግሊዝ ተሰርቀው የተወሰዱ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲመለሱ በማድረግ የአካባቢውን ታሪካዊነት ማስቀጠል ይገባል" ብለዋል፡፡

 በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ስፔናዊው እንድሪያስ ማርቲኔዝ በበኩላቸው በአውሮፓ ውስጥ በገናናነታቸው በስፋት የሚታወቁት አጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን የሰውበትን  ቦታ ፣ ቤተመንግስታቸውንና ሌሎች ታሪካዊ ቤቶች ፍርስራሽ ምልከታቸው  "የአካባቢውን ውበትና ስትራቴጂክ አቀማመጥ ለማድነቅ ቃላት ያጥረኛል" ብለዋል፡፡

 የንጉሱን መቃብር ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ እንክብካቤ እንዳለገኙ መመልከታቸውን አውስተዋል፡፡

 በወቅቱ በአካባቢው የነበሩትንና አሁን ፍርስረሳሻቸው የሚታዩ ቤቶችን እንደ አዲስ በመገንባት ታሪካዊነቱን ማጠናከር እንደሚገባ  ጠቁመዋል፡፡

 የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ዮኃንስ መቅደላ አምባን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በአምባው የሚገኙ ስምንት ታሪካዊ ቦታዎች ከሶስተኛ ወገን በማጽዳት የይዞታ ማረጋጋጫ ማግኘቸውን ገልጸዋል፡፡

 አቶ ኢያሱ እንዳመለከቱት በተጨማሪም  አምባው ላይ 9 ሚሊዮን ብር የሚወስድ የሙዚየም ግንባታ ለማከናወን የዲዛይን ስራ ተከናውኗል፡፡

 እስካሁን ለስራው ከአካባቢው ኅብረተሰብና ከመንግስት ከ600 ሺህ ብር በላይ መገኘቱን ጠቁመው፤በተለይ ባለሀብቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ታሪካዊውን ቦታ ከ150 ዓመት በላይ በማስከበርና በመጠበቅ የአካባቢው ኅብረተሰብ ላደረገው የላቀ አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸጸዋል፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ  ጋር በመተባባር አካባቢውን የማልማትና ቅርሶቹን የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

 ከገብኝቱ በኋላ በመቅደላ አምባ አካባቢ ዘጠኝ  የሚደርሱ ጥናታዊ ጽሑፎች በተጋባዥ እንግዶች የቀረቡበት ስብሰባ ተካሄዷል፡፡

 በስብሰባው የጎንደርና ሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ አርቲስቶችና ጥሪ የተደረጋላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን