አርዕስተ ዜና

በኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት አሁንም የጥራት መጓደል ችግር እያጋጠመ መሆኑን ደንበኞች ተናገሩ

12 Jan 2018
268 times

ባህር ዳር ጥር 4/2010 ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማዘመን እስከ ቀበሌ ድረስ የኔት ወርክ ማስፋፊያ ዝርጋታ ቢያካሂድም አሁንም የጥራት መጓደል ችግር እያጋጠመ መሆኑን ደንበኞች ተናገሩ።

ድርጅቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችና  መፍትሄው ዙሪያ ትናንት በባህርዳር ከሚገኙ ደንበኞች ጋር ተወያይቷል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቢስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የመጡት አቶ የሽዋስ ጥላሁን እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም የገጠሩ ህብረተሰብ የሞባይልና የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስፋፊያ ቢያካሂድም የአልግሎት ጥራት መጓደል አሁንም ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

በቅንጅት መጓደል ሳቢያም የተዘረጉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በየጊዜው እየተጎዱ ለአገልግሎት ጥራት መጓደል ችግር እየሆኑ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አስሜ ብርሌ የተባሉ ደንበኛ ናቸው።

እያጋጠመ ያለውን የኢንተርኔትና መሰል አገልግሎቶች ጥራት መጓደል ለማስተካከል  ድርጅቱ ከመንገድ፣ ከመብራት፣ ከውሃና መሰል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባል።

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ባልደረባ አቶ መላኩ ጥላሁን በበኩላቸው የመረጃና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ማዕከላቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ለሚያስገባቸው ዕቃዎች በቀላሉ መለዋወጫ የሚገኝላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለይቶ ስራ ላይ ማዋል አለበት" ብለዋል።

የደንበኞችን እርካታ ለመፍጠር ከመድረኩ የተነሱ ችግሮችን ተቀብሎ በቀጣይ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ብሩክ አድሃና ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳመለከቱት በቂ የመለዋወጫ አቅርቦት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስመጣት ስራ ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡

በተለይ በገጠር ቀበሌዎች የሶስተኛው ትውልድ የተባለው ኔት ወርክ አገልግሎት መስፋፋቱ ወጣቶች በቀላሉ ባሉበት አካባቢ ሆነው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።

የተዘረጉ የፋይበር መስመሮችም በልማት ምክንያት በአንድ በኩል ቢቆረጡ አገልግሎቱ ሳይሰናከል  በሌላ በኩል እንዲሰሩ የሚያስችሉ አሰራርን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ቀጥታ ያልሆነ ሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ይመር ተፈራ የሚስተዋለውን በኃይል ምክንያት  የኔት ወርክ መቆራረጥ ችግር ለመፍታት  133 አማራጭ ጄኔሬተር የመትከል ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ይህም ከመብራት መጥፋት ጋር ተያይዞም በመደበኛ ስልክ፣ በሞባይል፣ በኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ያስችላል ነው ያሉት አቶ ይመር።    

ሪጅኑ ከክልሉ መንግስትም ሆነ ከአጋር አካላት ጋር የሚያጋጥሙ የኔት ወርክ መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል። 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ