አርዕስተ ዜና

የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት 4 ሺህ ጠርሙስ መጠጥ ተያዘ

12 Jan 2018
297 times

ጅማ ጥር 4/2010 በጅማ ከተማ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት "በክለር" የተባለ መጠጥ ከማከፋፈያ ቤቶች መሰብሰቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡  

የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ አድናን ሻሚል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት 4 ሺህ ጠርሙስ መጠጥ ሊሰበሰብ  የቻለው  ፍተሻ ከተካሄደባቸው ሦስት የቢራ ማከፋፈያ ቤቶች በሁለቱ ላይ ተከማችቶ በመገኘቱ ነው፡፡

ከማከፋፈያ ቤቶቹ የተሰበሰበው መጠጥ  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2017 የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የመጠቀሚያው ጊዜ ያለፈበት ማንኛውም ምርት በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

"በጅማ ከተማ የተያዘው መጠጥ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል ሕብረተሰቡ ማንኛውም የታሸጉ ምግቦችና መጠጦችን ሲጠቀም የመጠቀሚያ ጊዜው ያላለፈ መሆኑንና ትክክለኛነቱን አረጋግጦ መግዛትና መጠቀም ይኖርበታል" ብለዋል።

ሕብረተሰቡ አጠራጣሪ ምርቶች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በፍጥነት እንዲያሳውቅም አቶ አድናን አስገንዝበዋል።

የኢዜአ ጋዜጠኛ በጅማ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ ሆቴሎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው የመጠቀሚያ ጊዜ አልፎበታል የተባለው መጠጥ አሁንም ለሽያጭ እየቀረበ መሆኑን ታዝቧል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ