አርዕስተ ዜና

ፍትሀዊ የሆነ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት ባለመኖሩ ተቸግረናል-- የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

12 Jan 2018
191 times

አርባምንጭ ጥር 4/2010 በአካባቢያቸው ፍትሃዊ የሆነ  የፍጆታ ምርቶች አቅርቦትና ስርጭት ባለመኖሩ መቸገራቸውን በአርባ ምንጭ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በዚህም ምክንያት በተለይም ስኳርና ዘይት ከገበያ ላይ በውድ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል ።

በአባያ ክፍለ ከተማ የመናኸሪያ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ታሪኩ እንደገለጹት በማህበራት አማካኝነት ለህብረተሰቡ እየቀረበ ያለው የፍጆታ ምርት ላይ እጥረት ከመኖሩ ባለፈ ፍትሀዊ የሆነ ስርጭት የለም።

አንዳንድ ማህበራት ለህዝቡ እንዲያከፋፍሉ የሚረከቧቸውን የፍጆታ ምርቶች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ነጋዴዎች  ስለሚያስተላልፉ ለዋጋ ንረት ችግር መጋለጣቸውንም ጠቅሰዋል።

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት አንድ ኪሎ ስኳር በ90 ብር እንዲሁም አንድ ሊትር ዘይት ደግሞ በ60 ብር ሂሳብ ከገበያ ላይ ለመግዛት ተገደዋል።

"በማህበራት በኩል የተፈቀደልን የፍጆታ ምርት መጠን ቀንሷል በሚል ሰበብ ለሶስት ቤተሰብ አባላት የተፈቀደውን ኮታ በአግባቡ እያገኘሁ አይደለም " ያሉት ደግሞ በነጭ ሣር ክፍለ ከተማ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሣራ ተፈራ ናቸው፡፡

ለህብረተሰቡ የሚቀርበውን ስኳርና ዘይት በህገ-ወጥ መንገድ ለነጋዴዎች አሳልፈው በሚሰጡ  ማህበራት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማርቆስ ፈለቀ በከተማው የግለሰብ ቤት የተከራዩ ነዋሪዎች ኩፖን ባለመውሰዳቸው የፍጆታ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡

በቀበሌው ለአምስት ዓመታት እንደኖሩ ያመለከቱት አቶ ማርቆስ በቀጠና ተጠሪዎች በኩል በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሶስት ጊዜ ቢመዘገቡም የፍጆታ ምርት መቀበያ ኩፖን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል ።

የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አበራ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የከተማው ነዋሪ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት መጠን ከተጠቃሚው ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን እንዳልቻለ ገልጸዋል ።

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ ከአምስት ዓመት በፊት በከተማው 29 ሺህ የነበረው የነዋሪ አባወራዎች ቁጥር አሁን ላይ ወደ 35 ሺህ ከፍ ሲል የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ከ600 ወደ 800 አድገዋል።

ይሁንና ለከተማው እየቀረበ ያለው 250 ሺህ ሊትር ዘይትና 2ሺህ 700 ኩንታል ስኳር ሊጨምር አለመቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

"የፍጆታ ምርቱም በ87 ቸርቻሪዎችና ማህበራት አማካኝነት በየወሩ እየቀረበ ነው " ብለዋል ።

በአሁኑ ሰዓት ተከራዮችን ታሳቢ ያደረገ የፍላጎት ጥናት ክለሳ ሥራ ተጠናቆ ለክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪ ቢሮ የቀረበ በመሆኑ በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝ አቶ ሀብታሙ አመላክተዋል ።

አንዳንድ ቸርቻሪዎችና ህብረት ሥራ ማህበራት ከግል ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሀብታሙ "በቅርቡ በስርጭቱ ላይ ፍትሃዊነት ባጎደሉ 13 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቷል " ብለዋል ።

እስካሁን ባለው የህግ ሂደት ሶስት ግለሰቦች እያንዳንዳቸው የአንድ ዓመት እስራትና የሁለት ዓመት ሽያጭ ገደብ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከተማው በያዝነው ወር ብቻ 1ሺህ 700 ሊትር ዘይት በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙንም አቶ ሀብታሙ ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ