አርዕስተ ዜና

በ18 ዩኒቨርሲቲዎች ሴቶች ከፍተኛ የአመራርነት ቦታዎችን ይዘዋል

12 Jan 2018
221 times

አዲስ አበባ ጥር 4/2010  በአገሪቱ ከሚገኙ 44 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በ18ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሴቶች ከፍተኛ የአመራርነት ቦታዎችን ይዘዋል።

ከፍተኛ አመራር የሚባለው ከምክትል ፕሬዚዳንት ጀምሮ እስከ ፕሬዚዳንትነት ያለው ቦታ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች ለፕሬዚዳንትነት በሚያወጧቸው ማስታወቂያዎች ሴት አመልካቾች አይታዩም።

አራተኛው አገር አቀፍ የትምህርት ልማት ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ሲጠናቀቅ በተደረገው ግምገማ በከፍተኛ አመራትነት ቦታ ሴቶች ምንም ድርሻ እንዳልነበራቸው ነው።

በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ማስታወቂያ በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ካመለከቱ 22 አመልካቾች መካከል ሴት አመልካች አልቀረቡም።

ከወራት በፊት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ማስታወቂያ በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ከቀረቡት ሰባት አመልካቾች  ሴት አንድ ብቻ ነበረች።

ከ2008 ዓም እስከ 2012 ዓ.ም በሚቆየው በአምስተኛው የትምህርት ልማት ፕሮግራም ሁሉም ዩንቨርሲቲዎች እያንዳንዳቸው ቢያንስ አንድ ሴት ከፍተኛ አመራር ሊኖራቸው እንደሚገባ እቅድ ቢኖርም በ26 ዩንቨርሲቲዎች ከፍተኛ የአመራር ቦታዎች በወንዶች ብቻ ተይዘዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ፆታ ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እስክንድር ላቀው እንደሚናገሩት በ18 ዩንቨርሲቲዎች ሴቶች ወደ ከፍተኛ የአመራርነት ቦታ ቢመጡም ከሚፈለገው አንፃር ቁጥሩ በቂ አይደለም።

ከትምህርት ፍትኃዊነት አንፃር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ ለማድረግና ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ለመስጠት የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

ሴት አመራሮች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማይመጡት በእውቀትና ክህሎት ክፍተት እንዲሁም ከአሰራርና መመሪያ ጋር በተያያዘ አይደለም ያሉት አቶ እስክንድር ተቋማቱ ከተለመደ አሰራር ባለመውጣትና በመልካም አስተዳደር ችግር የተነሳ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተሰራ ጥናት ባይኖርም በሚኒስቴሩ በሚደረጉ የክትትል ስራዎች ብቃት ያላቸው ሴቶች  በተለያዩ ችግሮች ወደ አመራርነት የሚመጡበት እድል አናሳ ቢሆንም ከአቅምና ከመመሪያ ጋር የተያያዘ ችግር የለም፤ ሴት አመራሮች የሉም የሚል ሀሳብ መኖር የለበትም ይላሉ።

ከዚህ በፊት ከነበረው ልምድ በመነሳት ሴት አመራሮችን በከፍተኛ አመራርነት ለማብቃት በአምስት አመቱ እቅድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአምስተኛው የትምህርት ልማት መርሃ ግብር መጨረሻ ተቋማት ቢያንስ አንድ ሴት ከፍተኛ አመራር ማካተት አለባቸው የሚለው እቅድ ለማሳካት በሚያስችል ፍጥነት እየተሄደ መሆኑን አቶ እስክንድር ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት በቦርድ አመራርነት የሴችን ተሳትፎ 25 በመቶ ማድረስ፣ ሴት አስተማሪዎችን ከነበረበት 12 በመቶ ወደ 25 በመቶ ከፍ ማድረግ፣ የሴት አመራሮች በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ከነበረበት 5 በመቶ ወደ 30 በመቶ  ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት አመራርነት የሚጀምረው ከማስተማር ስራ በመሆኑ በትምህርት ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን ሴቶች በዩኒቨርሲቲዎች አስተማሪ እንዲሆኑ በማድረግ የትምህርት እድል የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በትምህርት ክፍሎችና ኮሌጆች ኃላፊነት በመስጠትና በስራ ውድድር ጊዜ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ሴቶችን ለማብቃት በዩኒቨርሲቲዎቹና በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ