አርዕስተ ዜና

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሰራለን- የሚዛን ከተማ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

12 Jan 2018
197 times

ሚዛን ጥር 4/2010 በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን የሰጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ፡፡

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ- ጠበብት ቀለመወርቅ አጥናፉ ለኢዜአ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከትምህርት ተቋሙ ጋር ተቀራርበው ይሰራሉ ።

የዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው በተሻለ አስተሳሰብና ስብዕና እራሳቸውን መገንባት እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል፡፡

"ግጭት መፍትሔ ሳይሆን ለጥፋትና ውድቀት ይዳርጋል" የሚሉት የጉባኤው ሰብሳቢ አፍራሽ ተግባር በዩኒቨርሲቲው እንዳይከሰት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።

በኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የኃይማኖት አባት ቄስ ዮሐንስ ቦልተኖ በበኩላቸው "የትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን ለማሳካት እንዲችሉ የግጭት ምንጭ የሚሆኑ ስጋቶችን ቀድመው መፍታት ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

"ከዩኒቨርሲቲ ጋር በሰላም ዙሪያ አብረን እየሰራን ነው" ያሉት ቄስ ዮሐንስ በተቋሙ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልፀዋል ።

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሕብረት ቀበሌ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ባንጃ ጌዝ በበኩላቸው "የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰላም ተምረው ሀገርና ወገናቸውን እንዲያገለግሉ ከግጭት መራቅ አለባቸው " ብለዋል ።

አንዱን ከሌላው በመለያየት ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩና የተለየ አቋም ያላቸው ግለሰቦች ካሉ ለይቶ ወደ ትክከለኛ መስመር መመለስ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

"በዩኒቨርሲቲ ላይ የሚደርስ  ማንኛውም ጉዳት የሁላችንም ጉዳት ነው" ያሉት አቶ ባንጃ የአካባቢው ነዋሪዎች የተቋሙን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንደገለፁት የትምህርት ተቋሙ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ በመስራቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያስተጓጉል የሰላም ችግረ አጋጥሞት አያውቅም። ይኸው የጋራ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል ።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ