አርዕስተ ዜና

በበዓሉ ሰሞን ለሚከሰት የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል

04 Jan 2018
332 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 በገና በዓል ወቅት ለሚያጋጥም የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጥ አገር አቀፍ የጋራ ኮማንድ ፖስት ማቋቋሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።

በዓሉ ከመድረሱ በፊት ችግሩ ይከሰትባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በመለየት የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሳደግ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ለስራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አቅርቦት በማሟላት ከአስቸኳይ የጥገናና የቴክኒክ ሠራተኞች በተጨማሪ የበላይ አመራሩም በስራው ላይ እንደሚሰማራ ገልጿል።

ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ከሌሎች ተቋማት በውሰት ማምጣቱንም አክሏል።

እንደ አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ኃይል ከሚጠቀሙ የሲሚንቶና የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ባለቤቶች ጋር በመነጋገር በበዓሉ ዋዜማ ማታ ኃይል መጠቀም እንዲያቋርጡ ሊደረግም ይችላል ሲል መግለጫው አትቷል።

ሌሎች ከፍተኛና መካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎችም በበዓሉ ዋዜማና ዕለት ኃይል ቀንሰው የመጠቀም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ኅብረተሰቡ ለበዓሉ ዝግጅት ከቀን ይልቅ በሌሊት ቢጠቀም የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት እንደሚችል ጠቁሟል።

ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተገናኘ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ ሲፈልግም በነፃ የስልክ መስመር 905 መደወል ይቻላል ብሏል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ