አርዕስተ ዜና

ለሜትር ታክሲ አገልግሎት የካርድ ክፍያ አሰራር ተጀመረ

03 Jan 2018
410 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 ተጠቃሚዎች የሜትር ታክሲዎችን አፕሊኬሽን በመጠቀም በካርድ የሚፈጸም ክፍያ አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር ተጀመረ።

ኢታ ሶሉሽንስ እና ዳሸን ባንክ አገልግሎቱን በጋራ የሚሰጡበትን የካርድ ክፍያ አሰራር ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

የክፍያ ሥርዓቱ ከእጅ በእጅ የክፍያ ሥርዓት ውጭ የሆነና ተጠቃሚዎች ከዳሽን ባንክ በሚገዙት የሁለቱን ኩባንያዎች ዓርማ በያዘ ካርድ  አገልግሎት የሚያገኙበት ነው።

የኢታ ሶሉሽንስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ገብረህይወት እንደገለጹት ካርዱን የያዘ ደንበኛ በ"8707" ነጻ የስልክ መስመር ሲደውል ሜትር ታክሲው ያለበት ስፍራ ይደርስለታል።

አዲሱ የአሰራር ሥርዓት ህብረተሰቡ በታክሲ ጥበቃ የሚያባክነውን ጊዜ የሚቀርፍ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ በኪሎ ሜትር 13 ብር እንደሚያስከፍል የገለጹት አቶ ተመስገን ታክሲዎቹ በመዲናዋ ለታክሲ መዳረሻነት በሚመቹ ቦታዎች በየሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዝግጁ ሆነው እንደሚጠብቁ ነው ያስረዱት።

"8707" ነጻ የስልክ ጥሪ መስመርን መጠቀም ያስፈለገው አገልግሎቱን የሚሹ ደንበኞች 24 ሠዓት ያለምንም የኔትወርክ ችግር መደወል እንዲችሉ ታስቦ መሆኑን አክለዋል።

ታክሲ ፈላጊ ደንበኞች ታክሲዎች ተገልጋዮች ያሉበት ድረስ ለሚመጡበት ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም ነው ያሉት።

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ