አርዕስተ ዜና

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ2 ሺህ 200 የሕብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህግ አገልግሎት ሰጠ

03 Jan 2018
385 times

ጎንደር ታህሳስ 25/2010 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የገቢ አቅማቸው ዝቀተኛ ለሆነ ለ2 ሺህ 200 የሕብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህግ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።

 የህግ ትምህርት ቤቱ በማዕከላቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ትናንት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

 በእዚህ ወቅት እንደተገለጸው ዩኒቨርሲቲው አገልገሎቱን የሰጠው በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ባቋቋማቸው ነጻ የህግ ድጋፍ ማዕከላት በኩል ነው።

 የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አበበ አሰፋ እንዳስታወቁት በዞኖቹ 15 ነጻ የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ሕብረተሰቡን እያገለገሉ ነው።

 አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና የኤች.አይ.ቪ ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 "ለእነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳያቸውን እስከ ሰበር ችሎት በመውሰድ ትክክለኛ ፍትህ እንዲያገኙ ተደርጓል " ብለዋል ።

 እንደ አቶ አበበ ገለጻ ለሕብረተሰብ ክፍሎቹ የተሰጠው አገልግሎት በገንዘብ ሲሰላ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ነው ።

 የነፃ  ህግ  ድጋፉ መስጫ ማእከላቱ ህብረተሰቡን ከማገዛቸው ባሻገር የህግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተግባር ልምድ እንዲቀስሙ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም ገልጸዋል፡፡

 የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ  በበኩላቸው  "ዩኒቨርሲቲው ማዕከላቱን በገንዘብና በቁሳቁስ ከመደገፍ ጀምሮ የህግ ባለሙያዎች በመመደብ ጭምር ለሕብረተሰቡ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ነው " ብለዋል ።

 ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት እየተሰጠ ያለው የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በተደራጀ አግባብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ።

 በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮሚሽነር አቶ አበረ ሙጨ እንደገለፁት፣ የሕብረተሰቡን የህግ ግንዛቤ ለማሳደግ ተቋማቱ የንቃተ- ህግ ትምህርት በስፋት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

 የምዕራብ በለሳ ወረዳ ነዋሪ ቄስ አሰፋ ተገኘ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "ለጠበቃ የምከፍለው 15ሺህ ብር በማጣቴ አቁሜ የነበረውን የህግ ጉዳይ ማእከሉ ባደረገልኝ ነጻ ድጋፍ ቀጥዬ በፍርድ ቤት ፍትህ አግኝቻለሁ " ብለዋል ።

 "በደረሰብኝ የመኪና አደጋ በገንዘብ እጦት ምክንያት ጠበቃ አቁሜ ለመከራከር ባለቻሌ ማዕከሉ የህግ ባለሙያ በመመደብ ድጋፍ አድርጎልኛል" ያሉት ደግሞ አቶ ዘመነ አሳየኸኝ የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡

 በዞኖቹ በተቋቋሙት ማዕከላት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከ26ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመክፈል አቅም የሌላቸው የተለያዩ የሕብረሰብ ክፍሎች ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ማግኘታቸው ታውቋል።

 ለአንድ ቀን በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ የፍትህ አካላት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ተወካዮች እንዲሁም የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ኃላፊዎች፣ የህግ ተማሪዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ