አርዕስተ ዜና

በበዓሉ ገበያ ያልተገባ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል --- ጽህፈት ቤቱ

03 Jan 2018
307 times

አርባ ምንጭ ታህሳስ 25/2010 የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የአርባምንጭ ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች በሚደረገው የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ የነዋሪውን የኑሮ ሁኔታ እየተፈታተነ ይገኛል ፡፡

በቅርቡ የዶላር ዋጋ ማስተካከያን ተከትሎ እንደ አርባ ምንጭ ከተማ  የዋጋ ጭማሪ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪ አድርገው በተሰጣቸው ጊዜ ውሰጥ ያላስተካከሉ 41 የንግድ ተቋማትን በማሸግ እርምጃ በመወሰዱ ገበያው እየተረጋጋ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

ይሁንና የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ  እንደሚወሰድ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ሰሞኑን በተደረገው እንቅስቃሴ የንግዱ ማህበረሰብ የዋጋ ዝርዝር በግልጽ ቦታ እንዲለጥፍ ተደርጓል፡፡

ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን ለማስቆም በየቀበሌው ግብረ-ኃይል መቋቋሙን ጠቁመው ህብረተሰቡ ጭማሪ የሚያደርጉና የዋጋ ዝርዝር የማይለጥፉ ሲያጋጥመው ጥቆማ እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ነጭ ሣር ክፍለ ከተማ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሠማሩ ወይዘሮ ትዕግስት ዓባይነህ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ወጥ የሆነ አሠራር ባለመዘርጋቱ ምክንያት አንድ ዕቃ በተለያየ ዋጋ ሲሸጥ መቆየቱን ተናግረዋል ፡፡

"ሰሞኑን በተደረገው የጋራ ውይይት መሠረት እያንዳንዱን ዕቃ ዋጋ ዝርዝር ለጥፈን የምንሸጥ በመሆኑ ለግልጸኝነቱ መልካም ነው " ብለዋል፡፡

የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤትም በየጊዜው ክትትል እያደረገ በመሆኑ በነጋዴዎች መካከል የዕቃዎች ዋጋ ልዩነት እንዳይኖር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪና ሸማች የሆኑት  ወይዘሪት ይመኙሻል መልካሙ በበኩላቸው "ቀደም ብሎ ከነበረው  የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ በአንጻራዊነት አሁን መጠነኛ ቅናሽ ይታያል " ብለዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው ተግባራዊነቱ ግን በተወሰኑ  ነጋዴዎች ብቻ በመሆኑ  በዓሉን ተከትሎ ጭማሪ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የግብርና ምርቶች ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን የተናገሩት ደግሞ በሴቻ ክፍለ ከተማ የቤሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፋሲካ ጋልባ ናቸው፡፡

በዚሁም ጤፍ ቀደም ሲል አንድ ኪሎ 26 ብር ከነበረው አሁን  ወደ 17 ብር ፣ በቆሎ ከ13 ወደ 8 ብር ዝቅ ማለቱን በማሳየነት ጠቅሰዋል፡፡

"ነገር ግን አሁንም የሸቀጣሸቀጥ ዋጋ ላይ ብዙም ለውጥ የሌለ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ቁጥጥሩን ማጠናከር አለበት "ብለዋል ፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ