አርዕስተ ዜና

ረቂቅ አዋጁ በህግ የተሰጠኝን ኃላፊነት ይጋፋል-ኢንሳ Featured

03 Jan 2018
347 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሺያል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንደሚጋፋበት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ እንዲሁም የሳይንስ ፣ መገናኛና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትና ባለድርሻ አካላትን በኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሺያል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ ዙሪያ አወያይቷል።

በ1946 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲ ለአገሪቱ የፈጣንና ዘላቂ ልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስኬት አስፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ 'የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሺያል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ' በሚል ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።

ኤጀንሲው በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቷል።

በረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጁ ከቀረቡት የኤጀንሲው ስልጣንና ተግባራት ጥቂቶቹ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና ከህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሚመሳሰሉ ናቸው ተብሏል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ታዜር ገብረእግዚያብሄር ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የቀረቡ አንዳንድ ተግባርና ኃላፊነቶች ከእኛ ኤጀንሲ ጋር ተመሳሳይ ናቸው በማለት ተናግረዋል።

"የጂኦ ስፓሽያል ኢንፎርሜሽን መሰብሰብ፣ ማምረት፣ማከማቸት፣ ማስተዳደርና ማሰራጨት" የሚለው ተግባርና ሃላፊነት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተግባርና ሃላፊነት በመሆኑ መነሳት አለበት ብለዋል።

የተጠያቂነት ስርዓቱን በማዳከም መንግስትን ለኪሳራ ስለሚያጋልጡ ተመሳሳይ ስልጣንና ተግባር ለሁለት የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በአዋጅ መስጠት አይቻልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን መሀመድ ኤጀንሲው የማንኛውንም የመንግስት ተቋም ስልጣንና ተግባር አይወስድም ተመሳሳይነት ያለው ሃላፊነትም በአዋጁ አልተካተተም ብለዋል።

"የጂኦ ስፓሽያል ኢንፎርሜሽን መሰብሰብ፣ ማምረት፣ ማከማቸት፣ ማስተዳደርና ማሰራጨት" የአገሪቱን የስነ ምድር መረጃ ለመሰነድ እንጂ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ስልጣን መጋፋት አይደለም ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ይህንን ተግባር የሚያከናውነው ቁልፍ የመሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለመጠበቅ መሆኑንም አቶ ሱልጣን ጠቁመዋል።

"በሌሎች አካላት የሚሰሩ የጅኦ ስፓሺያል ስራዎችን መቆጣጠር" ሲባል ተቋሙ የሚሰራውን የስነ ምድር መረጃ በተመለከተ እንጂ በሌሎች ተቋማት ሃላፊነት ጣልቃ መግባት አይደለም ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ተቋማትም ተመሳሳይ ሀሳቦች አቅርበው ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ለምክር ቤቱ ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሏል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ