አርዕስተ ዜና

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አጠናክረን እናስቀጥላለን--- የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች

03 Jan 2018
307 times

ሀዋሳ ታህሳስ 25/2010በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ አጠናክረው ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰሩ የነዋሪ ተወካዮች፣ የሃዋሳ ከተማና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አስታወቁ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ላይ ስድስቱ የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ከተውጣጡ የሕብረተሰብ አካላት ጋር ትናንት ውይይት ተካሂዷል፡፡

ከሀዋሳ፣ ወንዶ ገነትና ይርጋለም ከተማ ከተውጣጡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተካሄደው ውይይት ላይ እንደተገለጸው በዩኒቨርሲቲው ያለው የመማር ማስተማር ሥራ ሰላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እየተካሄደ ነው።

በዩኒቨርሲቲው ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አጠናክሮ ለማስቀጠል " በየኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና የከተማው አመራሮች በጋራ መስራት አለባቸው " ተብሏል፡፡

ከይርጋለም ከተማ የሃይማኖት ተቋም ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ዘውዲቱ ጥላሁን ሁሉም ነገር የሚከናወነው ሰላም ሲኖር እንደሆነ ጠቁመው ችግር ቢከሰት የሚጎዳው ዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ህዝብ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስልክ ሳይቀር እየደወሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎል የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ኃይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው ሕብረተሰብና በአመራሩ የጋራ ጥረት የጥፋት ኃይሎች የሚያደርጉትን ቅስቀሳ ለመመከት በተከናወኑ ተግባራት ተማሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ ጉዱማሌ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አማን ገብረኪዳን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተማሪ አያያዙን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  ጠቁመዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አያኖ በራሶ እንደገለፁት በተቋሙ በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ 45 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 23 ሺህ 500 የሚሆኑት በግቢው ውስጥ የሚኖሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎቸ ናቸው፡፡

ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አቶ አያኖ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲውና ለከተማው ሰላም መረጋገጥ እርስ በእርስ በመደጋገፍ መስራት ይገባል።

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በበኩላቸው እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩና የጸጥታ ኮማንድ ፖስት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡

ሕብረተሰቡ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲን እንደራሱ ንብረት አድርጎ ስለሚያይ በተቋሙ ያለው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተማሪዎችን በመምከር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ያሉ የንግድ ተቋማት በመማር ማስተማር ሥራው ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽእኖ ለማስወገድ ጫት ማስቃሚያና ሺሻ ቤቶችን የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ