አርዕስተ ዜና

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የድርሻቸውን እንደሚሰሩ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ Featured

03 Jan 2018
327 times

ድሬዳዋ ታህሳስ 25/2010 በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተነሳ የወሰን ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በሚሰሩ ተግባራት የድርሻቸውን ኃላፊነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኃይማኖት አባቶች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮችና የሁሉም ኃይማኖቶች መሪዎች በድሬዳዋ ፣ በሐረርና በባቢሌ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ዛሬ መጎብኘት ጀምረዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በተፈጠረው ችግር ማዘናቸውን ገልጸው፤ተፈናቃዮች በአጭር ጊዜ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

መሰል ችግር ዳግም እንዳይከሰትም ሁሉም ለሰላም ዋጋ በመስጠት መስራት እንዳለበት የገለፁት ፓትሪያሪኩ ለተፈናቃዮቹ የእለት የምግብ ድጋፍና በዘላቂነት ለማቋቋም ቤተክርስቲያኗ የምታደርገው ድጋፍ በአስተባባሪው አካል በኩል እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ሼህ መሐመድ አሚን በበኩላቸው ከችግሩ መከሰት ጀምሮ በፀሎትና በመንፈስ ከተፈናቃዮች ጋር መሆናቸውን አስታውሰው እነሱን ለማቋቋም በሚደረገው ሥራ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም "የናንተ ተሳትፎ ታክሎበት በአጭር ጊዜ የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ህይወት እንድትኖሩ እንሰራለን" ብለዋል።

"ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በደረሰው ችግር አዝነዋል ፤ ከፌደራል መንግስት ፣ ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልል መንግስታት ጋር በመሆን የተሻለና ዘላቂ ህይወት እንድትኖሩ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ናቸው።

"በመጠለያ ጣቢያ ያላችሁ ወጣቶች በትምህርትና በሙያ ስልጥናችሁ ራሳችሁን የምትችሉበትን መንገድ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እናመቻቻለን ፤ከናንተም ጎን እንቆማለን"  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን ህብረት ፕሬዘዳንት ፓስተር ጻድቁ በበኩላቸው "በመጠለያው  ለሚገኙ የወለዱ እናቶች ፣ጨቅላ ህፃናት ፣አዛውንቶች ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በተቀናጀ መንገድ የተፈናቃዮች ህይወት በአጭር ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ  እንሰራለን" ብለዋል።

ዛሬ ጠዋት በድሬዳዋ አዲሱ ቄራ የሚገኘውን ጊዜያዊ መጠለያ የጎበኙት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎችና አመራሮች ከቀትር በኋላም በሚሊኒየም መናፈሻ የሚገኘውን መጠለያ  ጣቢያን ይጎበኛሉ።

በነገው እለት ከሁለቱ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች የሚገኙባቸውን የዳኬታ፣ የሃማሬይሳና የድሬ ጠያራን መጠለያ ጣቢያዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ