አርዕስተ ዜና

የጊኒዎርም በሽታን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ---ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን

07 Dec 2017
705 times

ጋምቤላ ህዳር 28/2010 የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን አሳሰቡ፡፡

 የጊኒ ዎርም በሽታ ማጥፋት ላይ ያተኮረ 22ኛው ሀገር አቀፍ የእቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል ።

 ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ባከናወናቸው ስራዎች በሽታው ለመጥፋት ተቃርቦ ነበር፡፡

 ሆኖም እንደገና አገርሽቶ በተያዘው ዓመት 14 ሰዎች በሽታው ተጠቅተው ተገኝተዋል፡፡ 

 በሽታው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአራት የአፍረካ ሀገራት በስተቀር በሌሎች የዓለም ሀገራት መጥፋቱን ፕሮፌሰር ይፍሩ ተናግረዋል ።

 ይሁንና በአራቱ የአፍሪካ ሀገራትም ቢሆን በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው እየቀነሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል

 መንስኤውም "በበሽታው አምጭ ረቂቅ ህዋስ የተበከለ ውሃ መጠጣት ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋል " ነው ያሉት።

 የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በሽታውን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት  ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 የዓለም ሎሬትና የአፍሪካ የጊኒ ዎርም ማጥፋት ፕሮግራም በጎ ፍቃድ አምባሳደር ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የበሽታውን መጥፋት የመጨረሻ ምዕራፍ ለማየት እቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል ።

 "ይሁንና በሽታው እንደገና በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ አስደንጋጭ ነው"ብለዋል።

 በተለይም ቀደም ሲል በጋምቤላ ክልል በተወሰኑ ወረዳዎች ብቻ ይገኝ የነበረው በሽታው  ዘንድሮ  ወደ ሌሎች አካባቢዎች የመስፋፋት አዝማሚያ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

 እንደ ዶክተር ጥበበ ገለፃ በተያዘው የአውሮፓ ዓመት በሽታው ይገኝባቸዋል ከሚባሉት አራት የአፍረካ ሀገራት መካከል በኢትዮጵያና በቻድ 28 ሰዎች ተጠቅተው ተገኝተዋል፤ በደቡብ ሱዳንና በማሊ ግን በበሽታው የተጠቃ ሰው አልተገኘም ።

 "ይህም በኢትዮጵያ በሽታውን በማጥፋት ረገድ ባለፉት ዓመታት የነበረው ስኬት ወደ ኋላ እየተመለሰ ስለመሆኑ አመላካች ነው" ብለዋል።

 የጊኒዎርም በሽታ ከሀገሪቱ  ለማጥፋት ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት የበሽታው ስርጭት ከክልሉ   ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 "ከህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስና ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅረቦት ችግር ጋር ተያይዞ በሽታውን የማጥፋቱን ስራ ጊዜ እንዲወስድ አድርጎታል" ብለዋል።

 በተለይም ባለፉት ዓመታት በሽታውን ለማጠፋት በተከናወኑ ስራዎች  የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ ሁለትና ሶስት ዝቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ የተጠቂዎች ቁጥር እንደገና ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

 ለሁለት ቀናት በተካሄደው ሀገር አቀፍ  የእቅድ አፈፃፀም መድረክ ባለድርሻ አካላትና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል ።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ