አርዕስተ ዜና

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር የፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናቶች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተባለ

07 Dec 2017
716 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ የሚያስችሉና ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮች እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት እና የስዊድኑ ጆንሾፒንግ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ትምህርት ቤት በጋራ ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው እሸቱ ጮሌ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል።

በኢኮኖሚክስና በቢዝነስ ዘርፍ ያሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የዘርፉ ምሁራንን በአንድ መድረክ በማገናኘት የእውቀትና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን ማቅረብ የጉባኤው አላማ ነው።

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ እንደተናገሩት፤ አገሪቷ በአሁኑ ወቅት ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሸጋገር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

በዚህ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በሚፈለገው መልኩ እንዳይሄድ ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንዳሉ ገልጸው፤ ለነዚህ ችግሮች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ማቅረብ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከአገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ የያዙት የግብርናና የአገልግሎት ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ "የኢንዱስትሪው በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ድርሻ ዝቅተኛ ነው" ብለዋል።

ኢንዱስትሪው ለአገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ለምን አነስተኛ ሆነ? የዘርፉን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ዙሪያ የኢኮኖሚ ምሁራን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ማቅረብ እንዳለባቸው ነው ዶክተር ይናገር ያስረዱት።

በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ላይ ያሉትን ችግሮች በጥናትና ምርምር በመለየት ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች ማስቀመጥ እንደሚገባና ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከግብርናው ዘርፍ  ወደ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በሚያደርጉበት ወቅት ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሆነ ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።

ስለዚህም የአፍሪካ የዘርፉ ተመራማሪዎች በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት በማካሄድ መንግስታት በቀጣይ መውሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በእውቀትና በመረጃ የተመሰረቱ ጥናቶችን ማድረግ የትኩረት አቅጣጫቸው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ይትባረክ ታከለ በበኩላቸው፤ በአገሪቷ ያሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች በየትኞቹ ላይ ጥናት ማድረግ ይገባል? ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ከመለየት አኳያ ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።

የክፍተቱ ምክንያት መንግስትና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀናጅቶና ተናቦ አለመስራት እንደሆነም ነው ዶክተር ይትባረክ ያስረዱት።

ጉባኤው መንግስትና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በማስተሳሰር በኢኮኖሚው ዘርፍ ሊጠኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች ለዘርፉ ምሁራን ከማመላከት አኳያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክትም አመልክተዋል።

በጉባኤው ላይ ከሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል በኤዲቶሪያል ቦርድ ተገምግመው ተገቢውን መስፈርት ያሟሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ጆርናል እንደሚታተሙ ጠቁመዋል።

በጉባኤው ላይ ከ22 አገራት የተወጣጡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዘርፉ ምሁራን እየተሳተፉ ሲሆን ከ80 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡም ተገልጿል።

ጉባኤው ነገ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ