አርዕስተ ዜና

በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ የተቋቋሙ ክበባት መቀዛቀዝ ለቫይረሱ ዳግም ማገርሸት አንዱ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ

07 Dec 2017
732 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 በኤች.አይ.ቪ ኤድስ  ዙሪያ የሚሰሩ ክበባት መቀዛቀዝ ለበሽታው ዳግም ማንሰራራት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር የአለም የኤድስ ቀንን አስመልክቶ  ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ ሴቶች ጋር ውይይት አካሄዷል።

የፅህፈት ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ እንደገለፁት ባለፉት አመታት በበሽታው የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር መቀነሱ  ህብረተሰቡ እንዲዘናጋና በሽታው ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጎታል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም  በየቀበሌውና ወረዳው ተቋቁመው የነበሩ ክበባት በሽታውን በመከላከልና ግንዛቤ በመስጠት የነበራቸው እንቅስቃሴ መዳከሙ ለበሽታው ማንሰራራት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመከላከል ክበባትን በማጠናከር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረው ህብረተሰቡም ተሳትፎውን በድጋሚ ማጠናከር እንደሚገባው ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ዋና ፀሃፊና የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዘነበች አበበ  በበኩላቸው በሽታውን የመርሳት ያህል ችላ በማለታችንና የሚገባውንም ትኩረት ባለመስጠታችን በድጋሚ ሊቀሰቀስ ችሏል ብለዋል።

ወጣት ሴቶች ለበሽታው ተጋለጭ መሆናቸውን አስታውሰው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት መቆም አለበት በማለት ተናግረዋል።

ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ዜጎች የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑም ተገልጿል፤ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ለሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች የተሻለ የስራ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ በውይይቱ የተገኙት ሴቶች አስታውቀዋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአገሪቷ 27 ሺ 288 ሰዎች በየዓመቱ በበሽታው የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 16 ሺ 21 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው::  

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ