አርዕስተ ዜና

በመዲናዋ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በየተቋማቱ የሚሰሩ ግለሰቦች በይቅርታ ጊዜው ውስጥ ራሳቸውን እንዲያጋልጡ ተጠየቀ

07 Dec 2017
721 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 በአዲስ አበባ ከተማ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ በየተቋማቱ እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦች በተቀመጠላቸው የይቅርታ የጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያጋልጡ ተጠየቀ።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 በሙስና ወንጀል እንደሚያስጠይቅና እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።

በመሆኑም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና የብቃት ማረጋገጫ እየሰሩ ያሉ ግለሰቦች ራሳቸውን ማጋለጥ እንዳለባቸው ነው የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ የገለጸው።

በአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ እንደገለጹት፤ ብቃት ያለውና ውጤታማ የሆነ ሲቪል ሰርቪስ ለመፍጠር የትምህርት ማስረጃዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች መኖራቸው ይታመናል። 

በዚህም በአዲስ አበባ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች "ከህዳር 7 እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ የይቅርታ ጊዜ ገደብ ተቀምጦ ራሳቸውን እንዲያጋልጡና ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርጓል" ብለዋል።

በመሆኑም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦች "በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ራሳቸውን ማጋለጥና ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል" ነው ያሉት።

በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሥራ የያዙና የደረጃ እድገት ያገኙ ሰዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ራሳቸውን የሚያጋልጡና ይቅርታ የሚጠይቁ ከሆነ በወንጀል እንደማይጠየቁ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ያለ አግባብ የወሰዱትን ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ መልሱ ሳይባሉ በትክክለኛ የትምህርት ማስረጃቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

እንደ ቢሮ ሃላፊው ገለጻ፤ የይቅርታ ጊዜው ከተጀመረበት ከህዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ቁጥራቸው ከ10 የማይበልጡ ሰዎች ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው መሆኑን በፈቃዳቸው አረጋግጠዋል።

የይቅርታ ጊዜው ከሚያበቃበት ከታህሣስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ መንግሥት በራሱ መንገድ አጣርቶ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲጠቀሙ ከደረሰባቸው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተገልጿል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ