አርዕስተ ዜና

መደኃኒቱን የተላመደ የቲቢ ህክምና ጊዜ ከሁለት አመት ወደ ዘጠኝ ወራት ዝቅ ሊል ነው

07 Dec 2017
419 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 መደኃኒቱን የተላመደ የቲቢ ህክምና አገልግሎት በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ መስጠት የሚያስችል አዲስ አሰራር መዘርጋቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በያዝነው ዓመት ከጥር ወር አንስቶ የሚጀመረው ይኸው አዲስ የህክምና አገልግሎት በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የቲቢና ስጋደዌ መርኃ ግብር አስተባባሪ ዶክተር ብሌን አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት መድኃኒቱን ለተላመደ የቲቢ በሽታ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ለሁለት ዓመት ይቆይ ነበር።

ያም ሆኖ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ የዓለም የጤና ድርጅት መድኃኒት ለተላመደ ቲቢ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ከዘጠኝ እስከ 11 ወራት ዝቅ እንዲል አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

ኢትዮጵያም መመሪያውን መሰረት በማድረግ አዲስ ጥምር መድኃኒቶችን በመጠቀም ለተላመደ ቲቢ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ዝቅ ለማድረግ መዘጋጀቷን ጠቁመዋል። 

ይህም ለቲቢ ህሙማን የሚሰጠውን ህክምና አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመስጠትና ታካሚዎች በጤና ተቋማት ለበርካታ ጊዜ እንዳይቆዩ ከመርዳቱ ባለፈ የታካሚዎችን ጫና እንደሚያቃልል ገልጸዋል።

አንድ ታካሚ በፊት ለ20 ወራት መደኃኒቱን ወስዶ አስኪጨርስ ድረስ መንግስት 50 ሺህ ዶላር ወጪ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ብሌን ይህም ታካሚው ህክምናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ጊዜውንና ለመደኃኒት ግዥ ይወጣ የነበረውን ወጪ በአራት እጥፍ እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

እንደሳቸው ገለጻ መደኃኒቱን በተላመደ ቲቢ በአዲስ መልክ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ነፍሰ ጡሮችና፣ ከሳንባ ውጭ መደኃኒቱን የተላመደ ቲቢ ያለባቸው ታካሚዎች እንደ በሽታው ክብደት ታይቶ የሚሰጥ  ነው።

አገልግሎቱን ለህሙማን መስጠት እንዲያስችል በየተቋሙ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን የማዘጋጀት፣ታካሚዎችን የመለየትና ተያያዥ ስራዎችን በቀጣዮቹ ሳምንታት እንደሚጠናቀቁም ዶክተር ብሌን ገልጸዋል።

አዲሱ ሕክምና በሚሰጥበት ወቅት የመድኃኒቱን የጎንዮሽ ጉዳት ለመቀነስ  ከኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል። 

መደኃኒቱን በተላመደ የቲቢ በሽታ በአዲስ መልክ የሚሠጠው ህክምና በሁሉም የጤና ተቋማት የሚሰጥ እንደሚሆን የገለፁት አስተባባሪዋ አንድ ሺ ሦስት መቶ ለሚሆኑ ህሙማን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ህክምና ለመስጠት እቅድ መያዙንም ገልፀዋል።

የቲቢ በሽታ በዓለማችን ከተከሰተ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ምርመራውም ሆነ ህክምናው የተጀመረው ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት ከዳረገና በዓለም ዙሪያ ስርጭቱ ከተስፋፋ በኋላ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ ስርጭት ካለባቸው 22 አገራት አንዷ ስትሆን በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ