አርዕስተ ዜና

ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን የፍራፍሬ፣ ቡናና ሰብል ምርታማነት ለማሻሻል እየሰራ ነው

07 Dec 2017
427 times

ሶዶ ህዳር 28/2010 የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በበጀት ዓመቱ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችን የፍራፍሬ፣ ቡናና ሰብል ምርታማነት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ ።

 ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ባቀረበላቸው የደጋ ፍራፍሬ ዝርያዎች ተጠቅመው ለውጥ ማምጣታቸውን የሃዲያ ዞን አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

 በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ታገሠ ለኢዜአ እንደገለጹት የምርታማነት ማሻሻያ መርሀ ግብሩ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አላማ ያደረገ ነው ።

 በሀዲያ ዞን በተመረጡ አራት ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው የፍራፍሬ፣ የቡናና የሰብል ምርታማነት ማሻሻል መርሀ ግብር ከ5 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

 እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በበጀት ዓመቱ ለሚከናወነው መርሀ ግብር ማስፈጸሚያ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል።

 እስካሁን በ48 ሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ ለአካባቢው አየር ንብረት የሚስማሙና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብልና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ መከናወኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 እንደ አፕል፣ ኮክና አቦካዶ የመሳሰሉ የተሻሻሉ የደጋ ፍራፍሬ ዝርያዎችን በስፋት ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

 "ለአርሶ አደሩ የክህሎትና የተግባር ስልጠና የሚሰጥባቸው አራት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት በማቋቋም አዳዲስ የፍራፍሬ ዝርያዎችን የማባዛትና የማላመድ ሥራም ተጀምሯል " ብለዋል ።

 ከዚሁ ጎን ለጎን  ከ450 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ በቆላማ  ቦታዎችም የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር የካርቦን ሽያጭ ለማካሄድ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

 "በመካከለኛው የዞኑ አካባቢም ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው ምርምር ውጤታማነቱ የተረጋጋጠ የተሻሻለ የገብስ ዝርያ  የማስተዋወቅ ሥራ እየተካሄደ ነው " ብለዋል።

 በሃዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማ ለገሰ " ቀደም ሲል ከዩኒቨርሲቲው የወሰድኳቸውን የተሻሻሉ የቡና፣ የአፕልና የአቦካዶ ዝርያዎችን  ተክዬ ተጠቃሚ ሆኛለሁ " ብለዋል ።

 የተሻሻለው የአፕል ዝርያ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት መስጠቱን የገለፁት አርሶ አደር ግርማ  ከአንድ ጊዜ ምርት ሽያጭ 9 ሺህ ብር ማግኘታውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 በዝርያ ማዳቀል የክህሎት ስልጠና ተጨማሪ ግንዛቤ በማግኘቴ በአነስተኛ መሬት በተከልኳቸው የአፕል ተክሎች መካከል ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን በመትከል ለቤተሰብ የምግብ ፍጆታና ለገበያ እያቀረብኩ ተጠቃሚ ሆኛለሁ " ሲሉም ተናግረዋል ።

 ሌላው በወረዳው የላምቡዳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብርሃም ሄሊሶ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ያገኟቸውን 40 እግር የአፕል ችግኞች ተክለው ከመጀመርያ ምርት ሽያጭ ከ15 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል ።

 "ባለፈው ክረምት ወቅት ከ10 በላይ 'ናቫል' የተሰኘ ቅባታማ የአቦካዶ ዝሪያ ችግኞችን ተክያለሁ "ብለዋል ።

 የሀዲያ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የጀመረው የምርጥ ዘር ብዜትና የደጋ ፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል ።

 እንደ ኃላፊው ገለፃ በደጋ ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ወደ ማምረት ደረጃ የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር የተካሄደ የገበያ ዳሰሳ ጥናት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ