አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የትግራይ ክልል ባህል ማህበር የተወሰዱ 122 ቅርሶችን አስመለሰ Featured

14 Nov 2017
949 times

መቀሌ ኅዳር 5/2010 የትግራይ ክልል ባህል ማህበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር 122 ጥንታዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዲመለሱ ማድረጉን አስታወቀ።

ማህበሩ በመቀሌ ከተማ ዘመናዊ የባህል ማዕከል ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

የትግራይ ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ከክልሉ በተለያዩ መንገዶች ወደ አውሮፓ አገራት ተወስደው የነበሩ 122 ጥንታዊና ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እንዲመለሱ ተደርጓል።

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የቀደምት ጥንታዊ ስልጣኔና የዘመን አቆጣጠር የሚገልጹ የብራና መጻህፍት ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪም ከወርቅ፣ ከብርና ከነሀስ የተሰሩ መስቀሎችን ጨምሮ የተለያዩ ቅርሶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

"ቅርሶቹ በመቀሌ አፄ ዮሐንስ ቤተመንግስት ሙዚየም ውስጥ በክብር ተቀምጠው ለጎብኚዎች እይታ እንዲውሉ ተደርጓል "ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቅርሶቹን በማስመለስ ሂደት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለ ድርሻ አካላትና የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ።

በተያያዘ ዜና ማህበሩ የክልሉ ሕዝብ ማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ አሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት፣ ለማስተዋወቅና ኪነጥበባዊ በሆነ መንገድ ለእይታ ለማብቃት የሚያገለግል የባህል ማዕከል በመቀሌ ከተማ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የመቀሌ ከተማ መስተዳድር ለማዕከሉ ግንባታ የሚሆን 50 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በነጻ መስጠቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የማዕከሉ የግንባታ ዲዛይን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በነጻ አየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ማዕከሉ ዘመናዊ ሙዚየም፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የቴአትርና ሙዚቃ ማሰልጠኛ፣ የባህልና ቋንቋ ምርምር ማዕከል፣ የህጻናት መዝናኛ ስፍራ ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ይኖሩታል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በህዝቡ፣ በተቋማትና በባለሀብቶች ትብብር የሚሸፈን ነው ።

ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የትግራይ ባህል ማህበር ለክልሉ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ መጎልበት አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን አስረድተዋል።

ከ36 ሺህ በላይ የማህበሩ አባላት ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ