አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በጋምቤላ ክልል የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

14 Nov 2017
544 times

ጋምቤላ ህዳር 5/2010 በጋምቤላ ክልል የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ  የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮና በዩኒሴፍ ትብብር የተዘጋጀ በእናቶችና ህጻት ጤና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኡማን አሙሉ እንደገለጹት በክልሉ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል፡፡

በክልሉ በተለይም በግንዛቤ ማነስ ፣ በጤና አገልግሎት ጥራት መጓደል እንዲሁም መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት ችግሮች ለእናቶችና ህጻናት ሞት ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የ2009 የስነ ህዝብና ጤና ጥናት ጠቅሰው እንደገለጹት በክልሉ ከሚወለዱት 1ሺህ ህጻናት መካከል 29ኙ አንድ ወር ሳይሞላቸው ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ።

እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በወሊድና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከሚሞቱት 412 እናቶች መካከል 46ቱ በክልሉ የሚመዘገብ ሞት መሆኑን ዶክተር ኡማን አመላክተዋል፡፡

የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ቢሮው በክልሉ በመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በመመደብ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን  ነው የጠቆሙት።

ችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ባለው ጥረት በክልሉ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በተለይ የእናቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ፣ ዩኒሴፍ፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ድጋፍቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በጋምቤላ ጤና ጣቢያ የእናቶች አዋላጅ ነርስ አዳሙ ጉዲና በሰጡት አስተያየት ነፍሰጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጤና ጣቢያው ሲመጡ ግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ብዙዎቹ ነፍሰጡር እናቶች በወሊድ ወቅት በቤታቸው እንደሚወልዱና ይህም በክልሉ ለሚታየው የእናቶች ሞት አንዱ መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

"ችግሩን ለመፍታት በተለይም በከተማው አካባቢ የሚገኙ እናቶች በጤና ጣቢያ በባለሙያ ተደግፈው እንዲወልዱ ለማድረግ ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በጋምቤላ ቅርንጫፍ የዩኒሴፍ አስተባባሪ አቶ ኦፒየው ኒክሰን በበኩላቸው ድርጅታቸው በክልሉ የሚታየውን የእናቶችና ሕጻናት ሞት ለመቀነስ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለእዚህም የተለያዩ መድኃኒቶችን ከማቅረብ ባለፈ ለጨቅላ ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም ድርጅታቸው በጤናው ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀዋል፡፡

በክልሉ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ