አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በሚገባ እንዲገነዘብ የሀገርህን እወቅ ክበባትን ማጠናከር ይገባል - የሻሸመኔ ሀገርህን እወቅ ክበብ አባላት

14 Nov 2017
588 times

ጎንደ ህዳር 5/2010 የሀገሪቱን  ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ትውልዱ በሚገባ እንዲገነዘብ በማድረግ ረገድ ሚና ያላቸውን የሀገርህን እወቅ ክበባት ማጠናከር እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሻሸመኔ ሀገርህን እወቅ ክበብ አባላት ተናገሩ፡፡

አባላቱ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት ወጣቱ ትውልድ ታሪኩንና ባህሉን እንዲጠበቅና እንዲንከባከብ በማድረግ ረገድ ክበባቱ የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡

የክበቡ አስተባባሪ ወጣት ብሩክ ይርጋለም ለኢዜአ እንደተናገረው በሻሸመኔ ከተማ ከተቋቋመ 10 አመታትን ያስቆጠረው ክበባቸው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን አባላቱ ተዘዋውረው እንዲጎበኙ አድርጓል፡፡

በእነዚህ አመታት እስከ 500 የሚደርሱ የክበቡ አባላት በተዘጋጁ የጉዞና የጉብኝት ፕሮግራሞች ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ እንዲያውቁ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብሏል፡፡

የህብረተሰቡን የጉብኝት ባህል በማሳደግ ረገድ ክበባቱ ትልቅ ድርሻ አላቸው የሚለው ወጣት ብሩክ በተለይ በትምህርት ቤቶችና በወጣት ማህበራት ክበባቱ እንዲጠናከሩና እንዲስፋፉ መደረግ እንዳለበት ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች መገኛ ሀገር በመሆኗ አካባቢንም ሆነ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች መጎብኘት ህብረተሰቡ ባህል ሊያደርገው ይገባል ያለችው ደግሞ የክበቡ አባል ወጣት አገሬ ጌቱ ነች፡፡

የክበቡ አባል ወጣት ብስራት ንጉሴ በበኩሉ የክበቡ አባላት የጉብኝት ዋና አላማ በሀገራችን የሚገኙ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ቦታዎችን በመጎብኘት ኢትዮጵያን ለተቀረው የሀገሪቱ አካባቢ ማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በርካታ ያልተነገሩ፣ ያልተሰሙና ያልተጎበኙ ታሪኮች አሉን የሚለው ወጣት ብስራት የሀገርን እወቅ ክበባት በማጠናከር የህብረሰቡን የመጎብኘት ባህል ማሳደግ ይገባል ብሏል፡፡

ጎንደር የጥንታዊ፣ ታሪክና ባህል ባለቤት ከመሆኗም በላይ የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ባህል እጅግ የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው ሲሉም የክበቡ አባላት ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ የመጀመሪያው ሩብ አመት የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትንና ሌሎች በከተማው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከ23ሺ በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውን ከከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ