አርዕስተ ዜና

በአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሚሰማሩ ወጣቶች ስልጠና ተሰጠ

14 Nov 2017
545 times

መቀሌ ህዳር 5/2010 የመቀሌ ዩኒቨርስቲ በሚያዘጋጀው የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር ላይ ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ ለተመለመሉ ከ1ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

 የዩኒቨርሲቲው  የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተርና የውድድሩ አስተባባሪ ዶክተር ከሳቴ ለገሰ እንዳሉት ከሰኔ 24 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሚያዘጋጀው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድር ላይ 7ሺህ ስፖርተኞች ይሳተፋሉ፡፡

 ለስፖርተኞቹ ተገቢውን የመስተንግዶ አገልግሎት የሚሰጡ ከ1ሺህ በላይ ወጣቶች ተመልምለው የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 ወጣቶቹ እንግዶችን በመቀበልና በማስተናገድ አምባሳደር ሆነው እንዲያገለግሉ  ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው የደቡብ ኮሪያ ባለሙያዎች አማካኝነት በበጎ አደራጎት ፅንሰ ሃሳብና ተግባር ላይ ያተኮረ የሁለት ቀን ስልጠና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

 በእንግዳ አቀባበል ስነ ስርዓትና በመጀመሪያ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰልጠናቸውንም ተናግረዋል።

 የዩኒቨርሲቲው  ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዓብደልቃድር ከድር እንደገለፁት ወጣቶቹ በፈቃዳቸውና በራሳቸው  ተነሳሽነት  በውድድሩ ለሚሳተፉ እንግዶች  አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸው የሚበረታታ ነው ።

 በደቡብ ኮሪያ የወጣቶች አለም  አቀፍ በጎ ፈቃደኞች ልኡካን አስተባባሪ ዶክተር ዩቦንገ ቹንግ  በበኩላቸው ስልጠናው ወጣቶች በስነልቦና ዝግጁ ሆነው  በፈቃዳቸው ነፃ አገልግሎት በመስጠት የሃገራቸውና የህዝባቸውን ፍቅር እንዲያዳብሩ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል ።

 የደቡብ  ኮሪያ ዓለም  አቀፍ የወጣቶች በጎ አድራጎት ድርጅት እንደ አውሮውያን አቆጣጠር በ2015 በደቡብ  ኮሪያ በተዘጋጀው የዓለም  ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ከ8ሺህ በላይ በጎፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን ያደረገ በጎ አድራጊ ድርጅት ነው።

 

  

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ