አርዕስተ ዜና

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ግንዛቤ ማስጨበጫ ትርኢት ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር ተጀመረ

12 Oct 2017
626 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የስደትን አስከፊነት በተመለከተ በሙዚቃ፣ በቴአትርና በጭውውት የሚቀርብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትርኢት ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር  ተጀመረ።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ ወጥ ስደትና አስከፊ ገጠመኞችን ተንተርሶ  ግንዛቤ የሚሰጠው አዝናኝ ትርኢት እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ እርከኖች እንደሚታይ ተገልጿል።

ትዕይንቱን የኔዘርላንድ ኤምባሲ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በጋራ አቅርበውታል።

በቀረበው ትርኢት ላይ ወጣት ሴትና ወንዶች እንዲሁም እድሜያቸው ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህፃናት በሕገ ወጥ ደላሎች አማላይነት ተታለው በጉዞ ላይ የሚደርስባቸው ስቃይና እንግልት ታይቷል።

ስደተኞች ከአገር ሲወጡ ለደላሎች ከሚከፍሉት በርካታ ገንዘብ በተጨማሪ ለግድያና ለአስገድዶ መድፈር ይጋለጣሉ።

"ደላሎች ሴቶችን ሜዲትራኒያን ባሕርን እናሻግራችኋለን" በማለት ገንዘባቸውን ከተቀበሉ በኋላ አስገድደው በመድፈር ለአካል፣ ለጤና እና ለስነ ልቦና ጉዳት እንደሚዳርጓቸውም የቀረበው ትርኢት አሳይቷል።

ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ የአመለካከት ችግር፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ የቤተሰብና የጓደኛ ግፊት ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚገፋፉ ድርጊቶች ናቸው።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምክትል ዐቃቤ ሕግ አቶ ተካ ገብረኪዳን በወቅቱ እንደገለጹት፤ ትርኢቱ ዜጎች የተሻለ ኑሮ በመፈለግ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው የሚደርስባቸውን ስቃይ "ኅብረተሰቡ በውል እንዲረዳውና እንዲገነዘበው ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።

"ኅብረተሰቡ ስለ ሕገወጥ  ስደት ያለውን ግንዛቤ ከማሳደግ በተጨማሪ፤ ሰዎችን ወደ ስደት የሚያማልሉ ሕገወጥ ደላሎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው" ብለዋል አቶ ተካ።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብር ኃይል በፈዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመውጣጣት ተቋቁሟል።

"የማይጨበጥ ተስፋ በመዝራት ዜጎች በአገራቸው ጥረው ግረው እንዳይለወጡ የሚያደርጉ ደላሎች የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር እንዲባባስ አድርገውታል" ያሉት አቶ ተካ፤ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግና ወንጀለኞች እንዲቀጡ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

የኔዘርላንድ ኤምባሲ ተወካይ ማርቲን ኮፐር በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዓለም አቀፍ መልክ የያዘውን ስደት ለመግታት እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ወርዶ መስራት ቀዳሚ ተግባር ነው። ሁሉም ሰው ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል መተባበር አለበት።

 ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ላይ ኅብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ  ለማሳደግ ወረዳዎች ድረስ በመውረድ በሙዚቃ፣ በቴአትርና በጭውውት መልክ ትዕይንት ለማቅረብ የኔዘርላንድ መንግሥት ፕሮጀክት መንደፉን ተወካዩ ገልጸዋል።

በቀጣይም ፕሮጀክቱ ስደት በስፋት በሚስተዋልባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች በመዘዋወር ትርኢቱን ለማቅረብ እንደተዘጋጀ ገልጸው፤ የኔዘርላንድ መንግሥትም በገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ