አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ጎጃም ዞን የተከሰተውን አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ለመከላከል እየተሰራ ነው

12 Oct 2017
606 times

ደብረ ማርቆስ ጥቅምት 2/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን የተከሰተውን አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ንብረት በሪሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት የአተት በሽታ በአሁኑ ወቅት በዞኑ 18 የገጠር ወረዳዎች ተከስቷል።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  ከዞን እስከ ወረዳ  አቢይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ነው።

በዞኑ በሚገኙ  ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ከ100 በላይ  የአተት ህሙማን ህክምና መስጫ ማዕከል ተቋቁሞና የባለሙያና ቁሳቁስ ተሟልቶ ህክምናው እየተሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እሰካሁንም ከ140 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በበሽታው ተይዘው ተገቢውን ህክምና በማግኘት ጤንነታቸው በመመለሱ ወደ ቤተቻው የተላኩ ሲሆን አራት ህሙማን አሁንም ህክምናውን በመከተታል ላይ ናቸው፡፡

ህብረተሰቡም የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅና ምግብን አብስሎ በመጠቀም ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በሽታው ከተከሰተም ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት መሄድና ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የአዋበል ወረዳ የለጋ ጤና ጣቢያ ሀኪም ሲስተር የምስራች ይርጋ እንዳሉት በአካባቢያቸው ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ ሁለት ሰዎች በበሽታው ተይዘው ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውንና ተገቢው ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

በዚሁ ወረዳ የእነሞጨር ቀበሌ ኗሪ አቶ ፈንታሁን ደጉ እንዳሉት ''ህመሙ እንደጀመረኝ  ፈጥኘ  ወደ ጤና ጣቢያ በመምጣቴ ህይወቴን ለማትረፍ ችያለሁ'' ብለዋል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ