አርዕስተ ዜና

ሰለማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በማጠናከር ለተሻለ ውጤት እንተጋለን - የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች

12 Oct 2017
1208 times

ጅግጅጋ ጥቅምት 2/2010 በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ሰለማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተግተው እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዩኒቨርሲቲው ነባር  ተማሪዎች ገለጹ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ነዋሪዎችና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ጋር በመሆን ለነባር ተማሪዎች ከትናንት ጀምሮ አቀባበል እያደረገ ነው፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የሲቪል ኢንጅነሪንግ ተማሪ አህመድዲን አደን በሰጠው አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ላደረገላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መደሰቱን ገልጿል፡፡

"የጅግጅጋ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይና ሰላም ወዳድ እንደሆነ ባለፈው አንድ ዓመት በሚገባ ተገንዝቢያለሁ፤ ዛሬም በተደረገው አቀባበል ያረጋገጥኩት ይህንኑ ነው" ብሏል፡፡

በዩኒቨርሲቲው አንዱ የሌላውን ባህል፣ ቋንቋና ማንነት አክብሮ በፍቅርና በሰላም ትምህርቱን እንደሚከታተል ገልፆ ይህ መልካም ተሞክሮ በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡

ከትግራይ ክልል የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የሶሺዮሎጂ ተማሪ ሄኖክ ገብረእግዚአብሄር በበኩሉ በመንገድ ላይ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠመውና በጅግጅጋ ከተማም ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው የተለየ ሁኔታ አለመመልከቱን ገልጿል።

ከደቡብ ክልል ሶዶ አካባቢ የመጣውና የሁለተኛ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ተማሪ አድማሱ አየለ  "በዩኒቨርሲቲው አቀባበል ከጠበቅኩት በላይ ሆኖ አግኝቻለሁ በዚህም ደስተኛ ነኝ" ብሏል፡፡

"እኔም ሆነ ቤተሰቤ ወደ ዩኒቨርሰቲው ስመጣ ስጋት ነበረብኝ፤ ሆኖም ከጅግጅጋ ከተማ እስከ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የገጠመኝ ቤተሰባዊ አቀባበል ስጋትና ጭንቀቴን አስወግዶታል" በማለት ተናግሯል፡፡

በትምህርት ቆይታው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል  የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

"በአካባቢያችን ጅግጅጋ ሳትደርሱ ችግር ሊገጥማችሁ ይችላል የሚል የስጋት ወሬ ነበር፤ ዛሬ እዚህ የተገነዘብኩት ፍጹም ተቃራኒና ሰላማዊ ነገር ነው" በማለት የተናገረው  ደግሞ ከደቡብ ክልል የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የ5ኛ ዓመት ሀይድሮ ኤሌክትሪክ  ኢንጅነሪንግ ተማሪና በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ተወካይ አንዱዓለም አስፋው ነው፡፡

"ሰላም ከሁሉም ይበልጣል፤ ለመማርም ሆነ ተመርቆ ለመውጣት ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በትምህርት ቆይታዬ ለሰላምና ለትምህርቴ ቅድሚያ እሰጣለሁ" ብላል።

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አቀባበል ሥነ ሥርአት ላይ የተገኙትና የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዲ ሙሴ ጅግጅጋ የተረጋጋች በመሆኗ ተማሪዎች ያለምንም ስጋት ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን አቶ ዩሱፍ መሐመድ ዩኒቨርሲቲው በ2010 የትምህርት ዘመን ለሚቀበላቸው ነባርና አዲስ ተማሪዎች ከክረምቱ ጀምሮ በቂ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኢልያስ ዑመር በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር፣ ከከተማው የሃገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በመተባበር ለነባር ተማሪዎች አቀባበል እያደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮ የትምህርት ዘመንም ከሦስት ሺህ 500 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ከጥቅምት 27 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚቀበል አስታውቀዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ