አርዕስተ ዜና

በትግራይ ደቡባዊ ዞን 85 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ

12 Oct 2017
782 times

ማይጨው ጥቅምት 2/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 85 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ ውሃ ማእድንና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ፡፡

 የመምሪያው ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ተሾመ ደበሳይ እንደገለፁት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት 54 የጎለበቱ ምንጮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 31 ደግሞ ከፍተኛና መካከለኛ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ናቸው።

 በውሃ ፕሮጀክቶቹ በዞኑ አምስት ወረዳዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው የገጠር ቀበሌዎች የሚገኘው ከ44 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

 በዚህም የዞኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ ከነበረበት 60 ነጥብ 3  ወደ 70 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉን አስታውቀዋል፡፡

 የመጠጥ ውሃ ተቋማቱ በአካባቢው የሚገኙ የቤት እንስሳት በበጋ ጊዜ የሚገጥማቸውን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለል ጭምር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

 ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ የየአካባቢው ነዋሪ ህዝብ አራት ሚሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት፤ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም አቶ ተሾመ አመልክተዋል።

 የእንዳመኾኒ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ መረሱ ሐለፎም በሰጡት አስተያየት በአቅራቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ቀደም ሲል የወንዝ  ውሃ  ለመቅዳት ረዢም ርቀት በመጓዝ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ  ለምርት ስራ ማዋል እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡

 ሌላው የራያ አዞቦ አርሶ አደር ረዳኢ ታደለ በበኩላቸው  በቀበሌያቸው የውሃ ጉድጓድ  ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ከቤተሰብ አልፎ  በበጋ ወቅት ያጋጥማቸውን የነበረውን የእንስሳት መጠጥ ውሃ እጥረት  እንደሚቀርፍላቸው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

 በዞኑ ባለፉት ዓመታት ከአንድ ሺህ 800 በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ