አርዕስተ ዜና

የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል ህብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ Featured

12 Oct 2017
279 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ጥሪ አቀረቡ።

 ቀዳማዊት እመቤቷ ከታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና አትሌቶች ጋር በመቀንጨር ችግርና በስርዓተ ምግብ ዙሪያ ተወያይተዋል።

 በአገሪቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት መካከል 38 በመቶው የመቀንጨር ችግር አለባቸው። መቀንጨር ባልተስተካከለ ስርዓተ ምግብ ምክንያት የሚመጣ የሚከሰት ነው።

 መቀንጨር በሕፃናት ጤንነትና የትምህርት አቀባበል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደር ባሻገር አምራች ዜጋ በመፍጠር ሂደት ላይ ተግዳሮት ይፈጥራል።

 ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የመቀንጨር ችግርን ማስወገድ የሁሉም ኃላፊነት ቢሆንም በተለይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና  ታዋቂ ግለሰቦች መልዕክቱን በማስተላለፍ በኩል የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

 "ችግሩ ሀገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ በአካልና በአዕምሮ ዳብሮ እንዳያድግ የሚያደርግ ነው፤ በመሆኑም እነዚህ ታዋቂ ሰዎች ያላቸውን ተደራሽነት በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ላይ ሊሳተፉ ይገባል" ነው ያሉት።

 መንግስት የመቀንጨር ችግር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን በማመን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት አድርጓል።

 የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው በአገሪቱ የመቀንጨር ችግርን ለማስወገድ ብሔራዊ የስርዓተ ምግብ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

 በሚኒስቴሩ የስርዓተ ምግብ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር አወቀ ከበደ በበኩላቸው የመቀንጨር ችግር አንዲት እናት ከፀነሰችበት ቀን አንስቶ ልጁ ሁለት አመት እስከሚሞላው ባሉት አንድ ሺህ ቀናት በሚኖረው የአመጋገብ አለመስተካከል እንደሚከሰት ገልጸዋል።

 በእርግዝና ወቅት የእናቲቱን ምግቦች የተመጣጠኑ በማድረግና ከወለደችም በኋላ እስከ ስድስት ወር በተከታታይ ጡት እንድታጠባ፣ ከዚያም ተጨማሪ ምግቦችን በአግባቡ ለልጇ እንድትሰጥ በማስቻል ችግሩን ማስወገድ ይቻላል።

 የውይይቱ ተሳታፊዎች ስርዓተ ምግብን አስመልክቶ በተደረገላቸው ገለጻ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ገልጸው መቀንጨርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ