አርዕስተ ዜና

በጤና ጣቢያዎቹ የተጀመረው በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት የእናቶችን እንግልት አስቀርቷል

12 Oct 2017
309 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 በአዲስ አበባ ፈለገ መለስና ኮልፌ ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ ያለው በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት ከእንግልትና ሊደርስባቸው ከሚችል የጤና እክል እየታደጋቸው መሆኑን እናቶች ገለጹ። 

በጤና ጣቢያዎቹ የቅድመ ወሊድ ክትትል ላይ የሚገኙ እናቶች ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል በወሊድ ወቅት የቀዶ ህክምና ቢያስፈልግ አገልግሎቱ ባለመኖሩ ወደ ሆስፒታሎች ይላኩ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ጤና ጣቢያዎች በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት በመጀመሩ ከእንግልትና በጤናቸው ላይ ሊደርስ ከሚችል አደጋ ስጋት እንዳላቀቃቸውና በዚህም ደስተኞች እንደሆኑ ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ሰሚራ ወልዴ በሰጡት አስተያየት የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ የኦፕራሲዮን አገልግሎቱ አልተጀመረም ነበር ክትትል አድርጌ ሪፈር ወደ ሌላ ነበር አሁን ግን ጤና ጣቢያው አገልግሎቱ በማሟላቱ እዚሁ እወልዳለሁ ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ወርቅነሽ አለሙ በበኩላቸው “አገልግሎቱን ከክፍያ ነፃና በአቅራቢያዬ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ “ብለዋል፡፡

በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት የሚሰጡት የፈለገ መለስ እና የኮልፌ ጤና ጣቢያ ኃላፊዎች የቀዶ ህክምናው መጀመሩ የወሊድ አገልግሎት መጠኑን ከእጥፍ በላይ አሳድጎታል ይላሉ።

የፈለገ መለስ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ በዳዳ ቀደም ሲል በጤና ጣቢያው በአንድ ወር የሚወልዱ እናቶች ከፍተኛው ቁጥር 30 ሲሆን አሁን በአማካይ እስከ 75 መድረሱን ተናግረዋል።

ይህም ወደ ሆስፒታሎች የሚላከውን የሪፈራል ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን ነው ያስረዱት።

ባለፉት ስምንት ወራት በጤና ጣቢያው 154 እናቶች በቀዶ ህክምና እንዲወልዱ መደረጉንም ገልጸዋል።

በኮልፌ ጤና ጣቢያ የበሽታ መከላከል ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ ቸርነት ኃይለሚካኤል ባለፉት ሶስት ዓመታት ለ1 ሺህ 20 እናቶች የቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎት መሰጠቱን ይናገራሉ።

ቀደም ሲል በወር እስከ 120 እናቶች በጤና ጣቢያው የሚገላገሉ ሲሆን አሁን ግን ቁጥሩ ወደ 300 ከፍ ብሏል ነው ያሉት።

የፋይናንስ እጥረት፣ የቀዶ ህክምና ግብዓቶችና የአንዳንድ መድሃኒቶች እጥረት መኖሩንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኤ ከወላድ እናቶች 35 በመቶ የሚሆኑት የቀዶ ህክምና እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ።

እናቶች ወደ ሌላ የጤና ተቋም ሳይላኩ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ጣቢያዎች ህክምናውን ማግኘታቸውን "የ2 ኪሎ ሜትር ርቀት ልዩነትም ከእናቶችና ልጆች ደህንነት አንጻር ትልቅ ለውጥ አለው" ሲሉ ገልፀውታል።

ስለሆነም ኮሌጁ በኮልፌና ፈለገ መለስ ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎት እንዲጀመር እገዛ አድርጓል ብለዋል።

እንዲሁም በኮሌጁ የሚገነባው የእናቶችና የህጻናት ክፍል ህንጻ እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ