አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማት ግንባታ መጓተቶችን ለማስወገድ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ነው

12 Oct 2017
278 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 በጤና ተቋማት ግንባታ የሚስተዋሉ የመዘግየት ችግሮችን ለማስወገድ እርምጃዎችን እየወሰደና የአቅም ግንባታ ስራ እያከናወነ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ፣ የጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የጫንጮ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች መሰረተ ልማቶች ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስጎብኝቷል።

የሆስፒታሎቹ የድንገተኛ፣ የልብ፣ የእናቶችና ህጻናትና የቀዶ ህክምና እንዲሁም የላቦራቶሪ፣ የራጅና የፅኑ ህሙማን ክፍሎች በሚዲያ ባለሙያዎቹ ተጎብኝተዋል።

የሚኒስቴሩ የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ የማነህ እንደገለጹት በጤና ተቋማት የግንባታ ሂደት የሚታዩ መጓተቶችን መቅረፍ እንዲቻል በቅድሚያ ችግሮቹ ተለይተዋል።

የግንባታ ዲዛይኖች መቀያየር፣ የኮንትራት አስተዳደር ችግር፣ የስራ ተቋራጮችና የአማካሪዎች አቅም ውስንነትና የግንባታ ግብዓቶች እጥረት ለጤና ተቋማቱ ግንባታ መጓተት በቀዳሚነት የተጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው።

በመሆኑም ሚኒስቴሩ ችግሮቹን መፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወንና እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኮንትራት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሰው ኃይል የማብቃትና የአደረጃጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የስራ ተቋራጮችና የአማካሪዎችን የአቅም ውስንነት ችግር ለማቃለልም ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ አክለዋል።

የግንባታ ግብዓቶች እጥረቱ ከውጭ አገር እቃዎችን ለመግዛት በሚያጋጥም የምንዛሪ እጥረት የሚፈጠር በመሆኑ ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ታደሰ ያብራሩት፡፡

የተጠቀሱትን ችግሮች በመፍታት የጤና ተቋማትን የግንባታ ጥራት ማስጠበቅና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በተጎበኙት የጤና ተቋማት የህክምና መሳሪዎች ያልተሟሉላቸውና ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ክፍሎችን ተመልክቷል።

ከ2006 - 2009 ዓ.ም የጤና መሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማስፋፋት ለተከናወኑ 2 ሺህ 215 ፕሮጀክቶች 13 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ