አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በአሶሳ ከተማ የምግብ ዋስትና እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብር ተጠቃሚዎች በወቅቱ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ገለጹ

13 Sep 2017
468 times

አሶሳ መስከረም 3/2010 በአሶሳ በከተማ ምግብ ዋስትና  እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብር ተጠቃሚዎች በወቅቱ ክፍያ ባለመፈጸሙ ለችግር መዳረጋቸውን  ተናገሩ።

በከተማዋ የገቢ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆነ የቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚዎችና በአካባቢ ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተለይተው ወደ ተግባራዊ ሥራ ከተገባ ሁለት ወራት አልፈዋል።

ይሁንና የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች አስካሁን ድረስ ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ እያገኙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ሮማን ወልደገሪማ በመርሀ  ግብሩ ተጠቃሚ  የከተማዋ  ነዋሪዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ  በከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥራ ማከናወን ከጀመሩ ከሁለት ወራት በላይ ቢያስቆጥሩም እስካሁን ድረስ ሙሉ ክፍያ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ካልተከፈላቸው ሥራውን ለረጅም ጊዜ ለማከናወን የሚያስችል አቅም የሌላቸው መሆኑን ኤጀንሲው  ተገንዝቦ  የቀረባቸው ክፍያ  እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሪት አልማዝ ጥላሁን  በበኩሏ፣  ከሁለት ወራት በላይ በደረቅ ቆሻሻ የማንሳት ሥራ ላይ ብትሰማራም በወቅቱ ክፍያ እያገኘች ባለመሆኑ ሥራውን ለመቀጠል እንደምትቸገርና ኤጀንሲው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቃለች።

ወይዘሮ ማማነሽ መኮንን የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመመረጣቸው ደስተኛ ቢሆኑም ድጋፉ እየተቆራረጠ መሆኑ ለችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።

በአሶሳ ከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የልማታዊ ሴፍትኔትና ኑሮ ማሻሻያ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እንዳሻው ይግዛው በበኩላቸው፣ ክፍያው በአሰራር ሂደት ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት የዘገየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየቀበሌው በተዋቀሩ ኮሚቴዎች የተመለመሉ ነዋሪዎች በትክክል ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው ስለመሆኑ ለማወቅ የተካሄደው የማጣራት ሥራ የወሰደው ጊዜ ለመዘግየቱ አንድ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

"ተጠቃሚዎችን በዘላቂነት ማቋቋም የመርሃ ግብሩ ዋንኛ ዓላማ በመሆኑ ከሚያገኙት ገቢ ሃያ በመቶ እንዲቆጥቡ ሁሉም ተጠቃሚዎች የቁጠባ ሒሳብ ደብተር እንዲያወጡ ለማድረግ የወሰደው ጊዜም ለመዘግየቱ ሌላው ምክንያት ነው" ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ተበድሮ የተወሰነ ክፍያ መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡

የተቀረውን ክፍያ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ በቀጣይ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ እንደሚፈጸምም አረጋግጠዋል።

የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎችን እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በአካባቢ ልማት በማሳተፍና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት በቀጣይ ተደራጅተው ራሳችውን እንዲችሉ ለማድረግ ኤጀንሲው በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በአሶሳ ከተማ ሦስት ሺህ 650 ነዋሪዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጨማሪ አምስት ከተሞችን በመርሃ ግብሩ ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙን የገለፁት አቶ እንዳሻው፣ የመርሃ ግብሩ ተግባራዊነት እስኪጠናቀቅ ድረስ 23 የክልሉ ከተሞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናገረዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ