አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እየተቸገሩ ነው

13 Sep 2017
477 times

ነቀምቴ መስከረም 3/2010 የጊምቢ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ለስምንት ዓመታት በመጓተቱ መቸገራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግሩ።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ቸርነት አስፋው እንደገለጹት የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ በ2002 ዓ.ም ሲጀመር በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም እስካሁን ባለመጠናቀቁ በውሃ እጥረት እየተጉላሉ ነው።

ለከተማዋ ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ነባሩ የውሃ ተቋም ከህዝብ ቁጥር ማደግ ጋር ተያይዞ በቂ ባለመሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ንፅህናው ያልተጠበቀ የወንዝ ውሃ ለመጠቀም ከመገደዱም ባሻገር በሴቶችና ህጻናት ላይ የሥራ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል።

"ለገጠሩ ሕብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተመቻቸበት በአሁኑ ወቅት የከተማ ነዋሪዎች ከእንስሳት ጋር እየተጋፉ የወንዝ ውሃ ለመጠቀም መገደዳቸው አግባብ አይደለም" ብለዋል።

የውሃ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠናቁ ለውሃ ወለድ በሽታ እየተጋለጡ መቸገራቸውን የገለጹት ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ ወይዘሮ ጌጠ ከበደ ናቸው።

መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ያስጀመረው ፕሮጀክት በትኩረት ማነስ በመጓተቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸው ችግሩ በተለይ በእናቶችና ሕፃናት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን አመልክተዋል።

የከተማዋ የውሃ አቅርቦት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ፕሮጀክቱ የሚጠናቀቅበት ሁኔታ እንዲመቻች የጠየቁት ደግሞ አቶ እጅጉ ኩሚ ናቸው።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃኔ ታመነ በበኩላቸው   በጊምቢ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቱን ተናግረዋል።

በተለይ የሥራ ተቋራጭ አቅም ማነስና የግንባታ እቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መናር በዋናነት ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከብዙ ድካም በኋላ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ቀሪውን ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ 26 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ ፣ የውሃ ማከፋፊያ ቦኖ ፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታና ሌሎችም ተጓዳኝ  ሥራዎችን ያካተተ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር ከ100 ሺህ ለሚበልጡ የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በጊምቢ ከተማ ቀደም ሲል የተሰራው የውሃ ተቋም ለ30 ሺህ ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እንደነበር ከዞኑ ውሃ ፣ መአድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ