አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ መሻሻል ታይቶበታል--- በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ተገልጋዮች

13 Sep 2017
426 times

ፍቼ  መስከረም 3/2010 አካባቢያቸው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ መሻሻል እየታየበት መሆኑን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች ገለጹ።

 የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ከ41 ሺህ  በላይ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን አስታውቋል።

 የፍቼ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዓለም ባይሳ በሰጡት አስተያየት በዞኑ ፍርድ ቤት በተለይ ከጥልቅ ተሀድሶ ወዲህ ለተገልጋዩ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት መሻሻል ታይቶበታል።

 ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤቱ በፍታብሄር ለታየ ጉዳያቸው ውሳኔ ለማግኘት 18 ቀጠሮ መፍጀቱን ያስታወሱት ወይዘሮ ዓለም በቅርቡ ከቤተሰብ ውርስ ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤቱ የታየው ጉዳያቸው በአራት ቀጠሮ ውሳኔ ማግኘቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 የደገም ወረዳ ነዋሪ  አቶ ታምሩ አረዶ በበኩላቸው በንብረት ይገባኛል ክርክር በወረዳው ፍርድ የተያዘው ጉዳያቸው በሦስት ቀጠሮ ብቻ እልባት ማግኘቱን ተናግረዋል ።

 " በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለከፈትኩት የፍታብሄር ክስ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ አግኝቻለሁ " ያሉት ደግሞ የገብረ ጉራቻ  ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃኔ አጋ ናቸው ።

 ከሁለት ዓመት በፊት በወረዳው ፍርድ ቤት ለተመሳሳይ የክስ መዝገብ የታየው ጉዳያቸው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በዘጠኝ ቀጠሮ ለውሳኔ መብቃቱን አስታውሰዋል ።

 ሌላዋ የግራር ጃርሶ ወረዳ ፍርድ ቤት ተገልጋይና የፍቼ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት አስጨናቂ በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ ለባለጉዳይ የሚደረገው አቀባበልና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

 የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑና በ13 ወረዳ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡ 44 ሺህ 104 የወንጀልና የፍትሐብሄር የክስ መዝገቦች ውስጥ 41ሺህ 39ኙ ውሳኔ ማግኘታቸውን  አስታውቋል።

 የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም አበበ እንደገለፁት ውሳኔ ካገኙት መዝገቦች ውስጥ 7 ሺህ 338ቱ የወንጀልና 33 ሺህ 701ዱ የፍታብሄር ናቸው ።

 " አብዛኞቹ የክስ መዝገቦችም በአጭር የጊዜ ቀጠሮ ውሳኔ ያገኙ ናቸው " ብለዋል ።

 ቀሪዎቹ ሦስት ሺህ 15 መዝገቦች ከወረዳ ይግባኝ  የተባለባቸውና ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው መሆኑንም አቶ አበርሀም ጠቁመዋል ።

 በበጀት ዓመቱ በፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ ያገኙ መዝገቦች ቁጥር በ2008 በጀት ዓመት ውሳኔ ከተሰጣቸው መዝገቦች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ 255  ብልጫ አለው።

 በበጀት ዓመቱ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ በአቅራቢያው ፍትህ እንዲያገኝ ተዘዋዋሪ ችሎትን በመሰየም ከወረዳ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ለተጠየቀባቸው 1 ሺህ 701  የክስ መዝገቦች  ውሳኔ መሰጠቱንም አቶ አብርሀም አስረድተዋል።

 እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ በተለይ በጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች ከህዝቡ የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ በተወሰደ የማስተካከያ እርምጃ በፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጥ ሂደት በመሻሻሉ ውሳኔ በመስጠት በኩል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

 በፍርድ ቤቶቹ ከተሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ