አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በሰሜን ወሎ ዞን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭት መልሶ እያገረሸ ነው

13 Sep 2017
264 times

ወልዲያ መስከረም 3/2010 በሰሜን ወሎ ዞን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭት መልሶ እያገረሸ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። 

በዞኑ ጤና መምሪያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ባለሙያ አቶ ኢዮብ ሰፊው እንደገለጹት  ካለፈው ዓመት ህዳር እስከ ሰኔ ባሉት ወራት በተመረጡ አምስት ከተሞች በተካሄደ ዘመቻ 43 ሺህ 623 ሰዎች የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አድርገዋል።

ምርመራ ካደረጉት መካከል 716 የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሲሆን ይህም በዞኑ የቫይረሱን ስርጭት ከ1 ነጥብ 6 በመቶ በላይ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የምርምራ ዘመቻው በሴተኛ አዳሪዎች ፣ በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ በቀን ሠራተኞችና በሌሎች ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ የተካሄደ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይ በሆስፒታል ደረጃ በተካሄደ መደበኛ ምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች በዘመቻ ከተካሄደው ከፍ ያለ መሆኑንም በጥናት መረጋገጡን አቶ ኢዮብ ገልጸዋል።

ኤች.አይ.ቪን የመከላከሉ ሥራ በበጀት አለመደገፉና አመራሩም በሽታውን የመከላከል ሥራ የጤና ተቋማት ብቻ አድርጎ ማየቱ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የደም ምርመራ ለማድረግ የሚያስፈልገው የምርመራ ኪት መጥፋቱ ለጋብቻ ቅድመ ምርመራ ማድረግ የሚፈልጉትን ጥንዶች እንኳ ማስተናገድ አለመቻሉንና የኮንዶም ስርጭቱም መቆሙም የራሱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ካለፉት አሥር ዓመታት ጀምሮ የፀረ ኤች.አይ.ቪ ሕክምና ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ሀብታሙ መኮንን ቀደም ሲል የነበረውን ጠንካራ የመከላከል ሥራ በመመለስ የተዘናጋውን ሕብረተሰብ መልሶ ማንቃት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እርሳቸውም በማህበራቸው አማካኝነት ወጣቱን በማስተማርና በመለወጥ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ከማድረግ በተጨማሪ በመከላከሉ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ እንዲደርግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

በወልድያ ከተማ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ያቋቋሙት " የተስፋ ብርሃን ማህበር" ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞላ ገበያው በበኩላቸው፣ በሽታው እንዳያገረሽ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት አንዳለባቸው አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽና ማጠናከር ዋና የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ውቤ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል ከፌደራል መንግስት ባለመላኩ የኮንደም አቅርቦት እጥረት ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት የአምስት ሚሊዮን ኮንዶም ግዥ በመከናወኑ ከፌደራል ወደ ባህር ዳር፣ ጎንደርና ደሴ ማከፋፈያዎች በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የመመርመሪያ ኪትም በቅርቡ ለተወሰኑ ለዞኖች የተሰራጩ ሲሆን ግዥ እስኪፈጸም ድረስ ይህንን ቅድሚያ ለተጋቢዎችና ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማዋል ችግሩን መቋቋም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ  ስርጭት በአማራ ክልል 1 ነጥብ 3 በመቶ  ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ 1 ነጥብ 18 በመቶ ላይ እንደሚገኝም ሃላፊው ተናግረዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ምጣኔ ከአንድ በመቶ በላይ ከሆነ በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ያሳያል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ