አርዕስተ ዜና

የመዲናዋ የመንገድ ሽፋን ወደ 6 ሺ 256 ኪ.ሜ አድጓል Featured

13 Sep 2017
523 times

መስከረም 2/2010 ባለፉት አስር  አመታት የአዲስ አበባ ከተማ  የመንገድ ሽፋን ከ 2 ሺ 537 ኪ.ሜ  ወደ  6 ሺ 256  ኪ.ሜ  ማደጉን  የከተማው መንገዶች  ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ይህ ደግሞ 9.4 በመቶ  የነበረውን የመንገድ ሽፋን ወደ  23.43  በመቶ  ያደርሰዋል፡፡

የከተማው  ነዋሪዎች በበኩላቸው የመንገዶች መስፋፋት የትራፊክ አደጋ ስጋትና ተያያዥ ችግሮች  እንዲቀረፉ አስችሏል  ብለዋል፡፡            

የከተማው መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጡማይ  ወልደገብርኤል  ለኢዜአ እንደገለፁት  ባለፉት አስር   አመታት   ባለስልጣኑ   የከተማውን    የመንገድ  ሽፋን   ለማሳደግ   ባከናወናቸው ተግባራት  የአስፋልት  መንገድን  1 ሺ 49  ኪ. ሜ   ወደ  ሁለት ሺ 709 ኪ.ሜ፣ የጠጠር መንገድን   ከ1 ሺ 488 ኪ.ሜ  ወደ 1 ሺ 508 ኪ.ሜ  በማሳደግ፣ የኮብል  ስቶን  መንገድን ደግሞ ምንም  ካልነበረበት  ሁለት  ሺ 38 ኪ.ሜ   መሥራት ተችሏል፡፡

የከተማው ነዋሪ አቶ ስዩም ወርቁ እንደተናገሩት ከብስራተ ገብርኤል ወደ መካኒሳ   የሚወስደው መንገድ ከመሰራቱ  በፊት የትራፊክ አደጋ  ስጋትን ጨምሮ በተለይ  ክረምት  ውሃ በመቋጠር ተሽከርካሪዎች  ሲያልፉ  ውሀ  በመርጨት እግረኛውን የሚያማርሩ ቢሆንም  ማስፋፊያ   ከተሰራ በኋላ ግን ችግሩ ተቀርፏል፡፡

“የቀለበት  መንገዶችን   ጨምሮ  ልዩ ልዩ  መንገዶች  መሰራታቸው   ከተማዋን  ልዩ  ውበት  እንድትጎናጸፍ  አስችሏታል” ያሉት ደግሞ  አቶ ተስፋሁን አሰፋ ናቸው፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ  ዳኜ  አሻግሬ ከራስ መኮንን ቅድስተ ማሪያም የሚወስደው መንገድ ማስፋፊያ ሳይሰራ እግረኛና ተሽከርካሪ  እየተጋፋ የሚተላለፍበትና ለአደጋ ተጋላጭ  እንደነበር ገልፀው  ማስፋፊያ ከተሰራ በኋላ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ከአደጋ ስጋት ነጻ   ሆነው  እየተላለፉ  ነው  ብለዋል፡፡

በመንገድ ግንባታው ዘርፍ በኮንትራክተሮች  ላይ  የሚታይ  የአቅም   ውስንነት፣ አልፎ አልፎ የሚታይ የጥራት  ችግርና  በወሰን  ማስከበር  ሂደት  የሚያጋጥሙ ችግሮች   ለፕሮጀክቶች መጓተት መንስኤ  መሆኑን  ዳይሬክተሩ  አመላክተዋል፡፡    

ህብረተሰቡ  መንገድን  እንደ  ውድ ሃብት አይቶ በአግባቡ ያለመንከባከብ፣ የተሰሩ   መንገዶችን   በአግባቡ ያለማስተዳደርና ሌሎች  ችግሮችም ይጠቀሳሉ፡፡ 

ችግሩን ለመቅረፍ ባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል  ጠንካራ  አስተዳደር  እንደሚዘረጋና ህብረተሰቡ  በመንገድ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን በመከላከል  በባለቤትነት  ሊጠብቅ  እንደሚገባም  አቶ ጡማይ   አሳስበዋል፡፡ 

ተሰርቶ ያለቀ መንገድ እንዳይቆፈር  ከባለድርሻ   አካላት ጋር  በቅርበት  ተናቦ   ለመስራት   ስምምነት  ላይ  መደረሱንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በሁለተኛው  የእድገትና ትራንስፎርሜሽን  እቅድ ዘመን  የከተማዋን  የመንገድ  ሽፋን 25 በመቶ  ከፍ  ለማድረግ  ታቅዶ  እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ከተሰሩ 16 ድልድዮች መካከል የጎላጎል አደባባይ፣ የፈረንሳይ ቀበና፣ የገርጂ  ሾላ ና   መገናኛ  አደባባይ የምእራብ  ድልድይ ይጠቀሳሉ፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ