አርዕስተ ዜና

በጋሞጎፋ ዞን በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 480ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል

12 Sep 2017
437 times

አርባ መንጭ መስከረም 2/2010 በጋሞጎፋ ዞን በክረምቱ ወራት ወጣቶች ባከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 480ሺህ ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኦፊሰር ወይዘሪት ናርዶስ ሺበሺ እንዳሉት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ282 ሺህ በላይ ወጣቶች በ23 የልማት መስኮች ተሳትፈዋል፡፡

ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናትና አረጋዊያን ድጋፍና እንክብካቤ፣ የደም ልገሳ፣ የጎልማሶች ትምህርት፣ የከተማ ጽዳትና ውበት ማስጠበቅ ወጣቶቹ ካከናወኗቸው  የልማት ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

ስራዎቹም ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸው ሲሆን 480ሺህ ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ወይዘሪት ናርዶስ ገልጸዋል፡፡

በጋሞጎፋ የካምባ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሽብሩ ሽርኮ አቅመ ደካማ በመሆናቸው በክረምት በተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶቹ የምግብና አልባሳት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

የተጎዳው መኖሪያ ጎጇቸውን ጭምር እንዳደሱላቸው በመጥቀስ ወጣቶቹን አመስግነዋል፡፡

በደንባ ጎፋ ወረዳ የዛንጋ አዋንዴ ቀበሌ ነዋሪው ተማሪ አድማሱ ካሌብ ወላጆቹን በሞት ካጣቸዉ በኋላ የሚያስተምረው ባለመኖሩ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዶ እንደነበር ገልጿል፡፡

በወጣቶቹ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎ የመማሪያ ደብተርና እስክሪቢቶ እንዲሁም ልብስ ጭምር ባደረጉለት ድጋፍ ያቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል መመዝገቡንም ጠቅሷል፡፡

ለጎልማሶች የተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት በክረምት በጎ አገልግሎቱን በማከናወኑ ደስተኛ መሆኑን የተናገረው ደግሞ  የሳውላ ከተማ ነዋሪና በሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት የሶስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው የሩቅነህ አውግቸው ነዉ ፡፡

" ሀገር የምታድገው በመንግስትና በህዝብ አንድነት በመሆኑ በጎ አገልጋይ በመሆኔ ነገ በሥራ ዓለምም ተግባሬን በሚገባ እንድወጣ የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማኝ አድርጎኛል" ብሏል ፡፡

የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪና በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ በስነ ህንጻ ጥበብ የሁለተኛ ዓመት ተማሪው አብርሃም ፍቃዱ በበኩሉ "በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፌ ጊዜዬን በአልባሌ ቦታ እንዳላባክን አግዞኛል" ብሏል ፡፡

በደም እጥረት ለሚቸገሩ ወገኖች  ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ደም መለገሱንም ጠቅሷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ