አርዕስተ ዜና

ፍርድ ቤቱ በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ ክስ እንዲመሰረት አዘዘ Featured

12 Sep 2017
806 times

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት አዘዘ።

በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር  ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩት በአቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ ሥር ያሉ 16 የሙስና ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ሆኖም ባሳለፍነው ዓርብ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካሪ የነበሩት አቶ ደጉ ላቀው በመካተታቸው ቁጥሩ ወደ 17 አድጓል። ፍርድ ቤቱ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት አዟል።

ፖሊስ የአቶ ደጉ ጉዳይ በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ ሥር ተጨምሮ እንዲታይ ያደረገበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱም አስረድቷል። በዚሁ መሰረት ተጠርጣሪው እስከ 500 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማድረሳቸውን አብራርቷል።

ከአቶ ደጉ በተጨማሪ ሁለት ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ የአቶ ደጉን ቃል አለመቀበሉንም በዝርዝር አስረድቷል። ይህንም በመጥቀስ ለተጠርጣሪዎች ዋስትና እንዳይሰጣቸውና ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።

ይሁን እንጂ ግራና ቀኙን የመረመረው ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትእዛዝ በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ  የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ  ክስ ተመስርቶ በመስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲቀርብ አዟል።

ቀሪ የምርመራ ሥራዎች በተሰጡት 11 ቀናት ውስጥ ጎን ለጎን እንዲከናወኑ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በወይዘሮ ፀዳለ ማሞ መዝገብ ሥር የሚገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች ላይም እስከ አርብ ድረስ ክስ ተመስርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ፖሊስ ተጨማሪ መያዝ ያለባቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉ፣ የፎረንሲክ ምርመራ እና የወጪ ማመሳከሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚቀርቡ ቢያስረዳም በፍርድ ቤቱ ውድቅ ሆኗል።

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ቀጠሮ ሲሰጥ የክስ ማቅረቢያ ቀን ቀንሶ መስጠቱን የገለፀው ፍርድ ቤቱ፤ እስከ አርብ ድረስ የክስ ማቅረቢያ ቀን ተሰጥቷል።

በጋራ የተጣመረው የአቶ ሲሳይ ሃይለሚካኤል እና የአቶ ታምሩ ታደሰ መዝገብን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ ያቀረበው የተጨማሪ የምርመራ ቀን ውድቅ በማድረግ እያንዳንዳቸው በ10 ሺ ብር ዋስ ወጥተው ጉዳያቸው በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ወስኗል።

ፖሊስ "ተጠርጣሪዎችን በዓይን አይቶ በመለየት ምስክርነቱን የሚሰጥ ምስክር አለኝ የቀጠሮ ቀን ይሰጠኝ" ቢልም፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ  የተጠርጣሪዎቹን ፎቶ በማሳየት ምስክሩን እንዲያስመርጥ ወስኗል።

ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ በማለቱ ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሐሙስ እንዲወጡ ያዘዘው ፍርድ ቤቱ፤ ተጠርጣሪዎች ከአገር እንዳይወጡም አግዷል።

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ "ከጠጠርና ብረታ ብረት በተያያዘ ከ20 ሚሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል" በሚል የተጠረጠሩት የእነ አበበ ተስፋዬ መዝገብ በነገው ዕለት እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት የእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብን ጨምሮ ስድስት መዝገቦችን ተመልክቷል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ