አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የቀጨኔ ታዳጊ ሴቶች ማቆያና ማቋቋሚያ ማዕከል ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም - አስተያየት ሰጪዎች

12 Aug 2017
490 times

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2009  በአዲስ አበባ የቀጨኔ ታዳጊ ሴቶች ማቆያና ማቋቋሚያ ማዕከል ውሰጥ የትምህርት መሳሪያዎች፣ የአልባሳትና የህክምና አቅርቦት ችግር መኖሩን የማዕከሉ ታዳጊ ሴቶች ተናገሩ።

 በማዕከሉ ተገቢ እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንዳልሆነም ታዳጊዎቹ አስታወቀዋል።

 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ስር የሚገኘው ማዕከል ቤተሰብ የሌላቸው፣ በጎዳና ወድቀው ለአደጋ ተጋላጭና ከሌሎች ህፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ለተዘዋወሩ እድሜያቸው ከ8 እስከ 18 ለሆኑ ሴቶች የመጠለያ፣ የምግብ፣ የትምህርት፣ የጤናና መሰል  አገልግሎቶችን ለመስጠት የተቋቋመ ነው።

 ማዕከሉ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ደረጃ የወጣላቸው ቢሆንም፤ በተቀመጠው መስፈርት እየተተገበሩ አለመሆኑን ታዳጊ ሕጻናቱ ይናራሉ።

 በተጨማሪም የሚደረግላቸው እንክብካቤ ቀድሞ ከነበረው ያነሰ መሆኑን ነው ታዳጊ ህፃናቱ ለኢዜአ የገለፁት።

 መስፈርቱን መሰረት በማድረግ በዓመት ሁለት ጊዜ ልብስ እንደማይገዛላቸውና ቢገዛም ዘግይቶ እንደሚደርሳቸው በማዕከሉ ያገኘናቸው ታዳጊ ትዕግስት ሽባባው፣ አይናለም ዘለቀና መቅደስ ወንደሙ  ተናግረዋል።

 ታዳጊ ሴቶቹ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በአካባቢው ባሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ቢሆንም ቶሎ እንደማይመዘገቡና የትምህርት ቁሳቁስም በአግባቡ እንደማያገኙ ጠቁመዋል።

 በተቋሙ የሚገኘው የህክምና ማዕከል የመጀመሪያ እርዳታ የሚሰጡ ሶስት ነርሶች ቢኖሩትም ተገቢውን ክትትልና የህክምና ድጋፍ እንደማያደርጉ ከታዳጊዎቹ ንግግር ለመረዳት ችለናል።

 ታዳጊዎቹ ተቋሙን ሲለቁ ለመቋቋሚያ የሚሰጣቸው 10 ሺህ ብር በቂ ባለመሆኑ ተመልሰው ወደ ጎዳና በመውጣት ላልተፈለገ እርግዝና እንደሚዳረጉ በተቋሙ ለስድስት ዓመታት ቆይታ የነበራት ወጣት ሃይማኖት ደበበ ገልፃለች።

 መቋቋሚያ ተብሎ የሚሰጠው ገንዘብ "ከቤት ኪራይ ባለፈ ለስራ ፈጠራ የሚውል አይደለም" ብላለች።

 ለመቋቋሚያ ከሚሰጠው የሙያ ስልጠና ጎን ለጎን ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ስራው እንዴት እንደሚሰራ የሚሰጥ ግንዛቤ  እንደሌለ ወጣቷ ተናግራለች።    

 የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት  የማህበራዊ ዘርፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እመይቱ ፀጋዬ  እንደሚሉት፤ ማዕከሉ የተሟላና ብቁ ሰራተኛ እንደሌለው፣ ነርሶች ቢኖሩም አገልግሎት በአግባቡ እንደማይሰጡ፣ ሴቶቹ በአንድ ክፍል ውስጥ ለመኖር ከተፈቀደው ቁጥር በላይ መሆናቸው፣ የተመጣጠነ ምግብ በአግባቡ እንደማያገኙ ተመልክተዋል።

 የተቋሙ ስራ አስኪያጅ አቶ ወላይ ፍስሃ በበኩላቸው እንደሚናገሩት 70 ሚሊዮን ብር አመታዊ በቂ በጀት የተመደበለት ሲሆን፤ የተባሉት ችግሮች አለመኖራቸውንና አገልግሎቱንም በተቀመጠው ደረጃ መሰረት እየሰጡ ናቸው።

 የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አለምፀሐይ ኤልያስ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ የተጠቀሱት ክፍተቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ ።

 አገልግሎቱን በተቀመጠው መስፈርት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ የተጠቀሱት ችግሮች የተፈጠሩት አቅራቢዎች ግዴታቸውን በወቅቱ ባለመወጣታቸውና ባለው የሰው ኃይል እጥረት እንደሆነም ገልጸዋል።

 የሚቀርቡት አልባሳትና የንፅህና መጠበቂያዎች ታዳጊዎቹ የሚፈልጉት አይነት እንዲሆኑ ተወካዮቻቸው ባሉበት እንደሚገዛ ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

 ኃላፊዋ እንዳሉት ችግሩን ለማቃለል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በመጋዘን የማከማቸት ስራ ተጀምሯል።

 በአጠቃላይ የመዋቅርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማስተካከል አዲስ ቢፒአር ተጠንቶ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

 የቀጨኔ ህጻናት ማቆያና ማቋቋሚያ ተቋም በ1944 ዓ.ም በእቴጌ መነን አማካኝነት ተቋቁማል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ