አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የአገልግሎት ጥራቱን ለማሳደግ የአሰራር ስርዓቱን እንደሚያሻሽል የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ

12 Aug 2017
443 times

አሶሳ ነሀሴ 6/2009 የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎችን በሚፈለገው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን ለማቅረብ የውስጥ አሰራሩንና የግዥ ሥርአቱን እንደሚያሻሽል የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብርሐም እንዳሉት በተያዘው አዲሱ በጀት ዓመት ኤጀንሲው የውስጥ አሰራሩን በማሻሻል አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ይሰራል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ብዙ ጊዜ እጥረት የሚከሰትባቸውን መሰረታዊ መድኃኒቶችን አቅርቦት ለማሻሻል ቴክኒካል ቡድን የማዋቀር ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ የመድኃኒቶችን የግዢ ሂደት ከመከታተል ባለፈ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በወቅቱ እንዲደርሱ ጥረት የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በእዚህም ባለፈው በጀት ዓመት 85 በመቶ የደረሰው የመሰረታዊ መድኃኒቶችን አቅርቦት በተያዘው በጀት ዓመትም 95 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አቅርቦት ለማሻሻልም ኤጀንሲው የአሰራር ስርዓት በመዘጋት ላይ ይገኛል።

ለእዚህም በቀላሉ የማይበላሹና በአነስተኛ ወጪ ሊገዙ የሚችሉ የሕክምና መሳሪያዎችን በራሱ ገዝቶ የሚያቀርብ ሲሆን ከፍተኛ ወጪና ቦታ የሚይዙ መሳሪያዎችን ደግሞ የሕክምና ተቋማትን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ግዢ ለመፈፀም ማቀዱን አስረድተዋል፡፡

ይህ አሰራር በተደጋጋሚና በተጠናጥል የሚፈጸሙ ግዢዎችን በማስቀረት ወጪንና ጊዜን መቆጠብ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ከኤጅንሲው ጋር ውል የሚገቡ አካላት ከአንድ ዓመት በታች የመጠቀሚያ ጊዜ ያላቸውን መድኃኒቶች ለመረከብ ፍቃደኛ አለመሆን መድኃኒቶች ከሚበላሹበት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ዶክተር ሎኮ ገልፀዋል፡፡

በሚሻሻለው የኤጀንሲው አሰራር የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሊያልፍ የተቃረቡ መድኃኒቶችን ለይቶ መድኃኒቶቹን ወደሚፈልጉ አካባቢዎች በማዘዋወር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደርጋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ ለሕክምና ተቋማት መድኃኒቶቹን በነጻ በመስጠትም ከብልሽት ለመታደግ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።  

ኤጀንሲው በ2009 በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዥ ፈፅሟል፡፡

ከግዢ ፣ ከነበረው ክምችት እንዲሁም ከአጋር አካላት ያገኘውን ድጋፍ በማካተት በአጠቃላይ በዓመቱ ከ13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አሰራጭቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ገዝቶ ለማሰራጨት ማቀዱንም ዶክተር ሎኮ ገልጸዋል።

በኤጀንሲው የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በአሶሳ ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ግምገማና ውይይት ትናንት ተጠናቋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ