×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ዩኒቲ ዩንቨርስቲ ለሶስተኛ ዲግሪ ስልጠና ዝግጅት መጀመሩን ገለጸ

29 Jul 2017
867 times

አዲስ አበባ አርባ ምንጭ/ሶዶ ሀምሌ 22/2009 ዩኒቲ ዩንቨርስቲ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በስምንት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ስልጠና እንደሚጀምር አስታወቀ።

ዩንቨርስቲው ለ34ኛ ጊዜ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም ያሰለጠናቸው 1 ሺህ 100 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳው በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት በቀጣዩ አመት በአዲስ አበባና በአዳማ ካምፓሶቹ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን ለመጀመር አቅዷል።

በሁለተኛ ዲግሪ ከሚከፈቱት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች መካከል በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ አግሪካልቸራል ኤኮኖሚክስ ፣አግሪ ቢዝነስ ፣ ቫሊው ቼይን ማኔጅመንት፣ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ ሊደርሺፕና መሰል መስኮች ይገኙበታል።

በመጀመሪያ ዲግሪ ደግሞ የሆርቲ ካልቸር ፕሮዳክሽንና ቴክኖሎጂ ስልጠና ፕሮግራሞች ይጀመራሉ ብለዋል።

በዛሬው እለት ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ ዴቬሎፕመንታል ኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፣ በኢንጂነሪንግ ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በጤና በግብርናና ሊደርሽፕ ፕሮግራሞች ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥም የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል ጥናት እያካሔደ መሆኑንም ዶክተር አረጋ ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በጤናው ዘርፍ የተሻለ አስተዋጽኦ ለማበርከት ሰላም የነርሲንግ ኮሌጅን ወደ ሜዲካል ኮሌጅ ለማሳደግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በዩንቨርስቲው ወደ 246 ለሚሆኑ ከታዳጊ ክልሎች የመጡ ፣የሳውዲ ተመላሾችና ከፍለው መማር የማይችሉ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ተሰጥቷቸዋል።

በመጪው አዲስ አመት መደበኛ የትምህርት እድል ያላገኙ ጎልማሶች በቀራንዩ ካምፓስ የነጻ ትምህርት እድልን መሰጠት እንደሚጀመርም ነው ዶክተር አረጋ ያረጋገጡት።

በሌላ ዜና የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ19ኛ ጊዜ 1 ሺህ 407 ተማሪዎችን ባሰመረቀበት ስነ- ስረአት ላይ የኮሌጁ ዲን አቶ በዛብህ ባርዛ እንደተናገሩት፣ ኮሌጁ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት የበኩሉን አየተወጣ ነው።

ለዚህም የዛሬዎቹን ጨምሮ 14 ሺህ 361 መካከለኛ ደረጃ ባለሙያዎችን ማስመረቁን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሰው ኃይል ልማት ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አጥናፉ አስፋው በበኩላቸው "ተመራቂ ተማሪዎች ባገኙት ዕውቀት ለለውጥ መዘጋጀት አለባቸው"ብለዋል ፡፡

በተመሳሳይ የወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዛሬ ያስመረቃቸው 792 ተማሪዎች ከደረጃ አንድ እስከ አምስት በዘጠኝ የቴክኒክና ሙያ መስኮች የሰለጠኑ መሆናቸውን ዲኑ አቶ ያሲን ቦቶ ተናግረዋል ።

" ኮሌጁ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማሸጋገር ለፈጣን ዕድገት ዕሴት የሚጨምሩ ብቁና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የማፍራት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ዥ" ብለዋል፡፡

በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ  ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ለልማት በማዋል ለሀገሪቱ እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ