አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ከአልኮል ነጻ የሙዚቃ ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

17 Jul 2017
674 times

አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2009 በአዲስ አበባ ከተማ እየከፋ የመጣውን  የመኪና አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ከአልኮሆል መጠጥ  ነጻ የሙዚቃ ፌስቲቫል በሚሊኒየም አዳራሽ ሐምሌ 19 ቀን ይካሄዳል።

የአዲስ አበባ መንገድ  ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከባለ ድርሻ እና ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን መድረኩን ያዘጋጀ ሲሆን ሐምሌ 19 ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ኤጀንሲው ይህን ያስታወቀው በዛሬው እለት የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች የሃይማኖት አባቶች፤የሾፌሮች ማኅበራትና የግል ተቋማት በተገኙበት በሰጠው መግለጫ ነው።

በዚህ አልኮሆል ሻጭና አልኮሆል ጠጭዎች በማይገኙበት የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ዳን አድማሱን ጨምሮ ሌሎች የሙዚቃ ሰዎችና ኮሜዲያን እንደሚገኙም ታውቋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ ገነቱ ደሳለኝ እንዳሉት በፌስቲቫሉ ቀን የአሽከርካሪዎችና እግረኞችን ግንዛቤ የሚያዳብር ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ይቀርባል።

ሰዎች መዝናናትን ሁልጊዜ ከመጠጥ ጋር ብቻ ያስቡታል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ቀን ሰዎች ሳይጠጡ መዝናናትና አስከፊ የሆነውን የመኪና አደጋና የሚያደርሰውን ሞት ለመቀነስ የሚያስችል  የውይይትና የግንዛቤ ቀን ይሆናል ብለዋል።

ዕለቱ "ጠጥቼ አላሽከረክርም" በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ከአልኮሆል ነጻ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ "በእኔ ምክንያት አደጋ አይደርስም" በሚል በቦታው የተገኙ ሰዎች ቃል የሚገቡበትና ቃላቸውንም በፊርማ የሚያረጋግጡበት ቀን ሆኖ እንደሚከበር ይጠበቃል።

በቦታው የተገኙት የኃይማኖት አባቶች እንደተናገሩት ጠጥቶ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ሳቢያ እየደረሰ ያለው አደጋ የሚያስከትለውን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቅረፍ በየቤተእምነታቸው በማስተማር የድርሻቸውን ያበረክታሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዳሉት መንግስት መንጃ ፍቃድ የሚያወጡ አሽከርካሪዎች ትክክለኛ የማሽከርከር ብቃት እንዳላቸው የሚያረጋግጥበትንና የሚከታተልበትን አሠራርና ቁጥጥር ማጠናከር ይገባዋል።

ከዚህ በተጨማሪ መጠጥ ጠጥቶ ማሽከርከር በሕይወትና በሀብት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ መከላከል ይቻል ዘንድ በቤተክርስቲያናቸው ለምእመናንና ለምእመናት እንደሚያስተምሩ ቃል ገብተዋል።

"የትራፊክ አደጋ አስከፊ ደረጃ ላይ ነው" ያሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተወካይ ሼህ አማን ሁሴን ሕዝበ ሙስሊሙ  በስፋት በሚገኝባቸው የእምነት ቦታዎች ሁሉ በማስተማር በአደጋው የሚደርሰውን ችግር ለመቀነስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው ከዚህ በተጨማሪ ከሐምሌ 23 ጀምሮ "ደሜን ለወገኔ እለግሳለሁ" በሚል መሪ ቃል ደም በመለገስ የ 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

መነሻውን አዲስ አበባ ስታዲዬም የሚያደርገው ይህ ሩጫ ደምበል አደባባይን ዞሮ ስታዲዬም ውስጥ ይጠናቀቃል ፤እዚያው ስቴዲዬም ውስጥ የታክሲ ሾፌሮችና ትራፊክ ፖሊሶች የእግር ኳስ ጨዋታ ያደርጋሉ።

የአንበሳ አውቶቡስ ሾፌሮች ዳኛ የሚሆኑበት ይህ  የእግር ኳስ ጨዋታ እያዝናና ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ተበሏል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ